ከባድ በተባለ ጥቃት ቦኮ ሃራም 92 የቻድ ወታደሮችን መግደሉ ተነገረ

የቻድ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻድ ፕሬዝዳንት 92 የአገራቸው ወታደሮች በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በተጸመ ጥቃት መገደላቸውን አስታወቁ።

ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ እንዳሉት ታጣቂው ቦኮ ሃራም ሰኞ እለት ጠዋት ላይ በፈጸመው ጥቃት ነው ወታደሮቹ የተገደሉት። ይህም በእስላማዊው ቡድን ባለፉት አምስት ዓመታት ከተፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ የአሁኑ እጅጉን የከፋ እንደሆነም አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በምዕራባዊ ቻድ አገራቸውን ከናይጄሪያና ከኒጀር ጋር የሚያዋስነውን አካባቢ ጎብኝተዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት ከናይጄሪያ የተነሳው የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ በአካባቢው ወዳሉ አገራት ከተስፋፋ በኋላ በደርዘኖች የሚቆጠሩ የቻድ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ደግሞ የናይጄሪያ መንግሥት እንዳስታወቀው የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ማይዱጉሪ ከተማ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 47 ወታደሮች ተገድለዋል።

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ይህንን ጥቃት የፈጸሙት ቦንብና ጥይቶችን ጭነው ከማይዱጉሪ ከተማ በመውጣት በአጀብ ሲጓዙ በነበሩ የናይጄሪያ ሠራዊት ተሽከርካሪዎች ላይ ነው።

የናይጄሪያ መንግሥት በመግለጫው ከተገደሉት ወታደሮቹ ውጪ በተፈጸመው ጥቃት ሸማቂው ቡድን ከተሽከርካሪዎቹ ላይ የወሰደው ወታደራዊ መሳራያዎች ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

ቦኮ ሃራም የሚባለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ውስጥ የመንግሥት ተቋማትንና ወታደሮችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ይታወቃል።

ቡድኑ ከናይጄሪያ ባሻገርም በጎረቤት አገራት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚፈጽም ሲሆን 92 ወታደሮቿ የተገደሉባት ቻድም ተደጋጋሚ ጥቃት ተፈጽሞባታል።