አማዞን የጆርጅ ፍሎይድን አሰቃቂ ሞት የሚያሳየውን ቲሸርት ከገበያ አስወጣ

የፎቶው ባለመብት, AMAZON
በሜኔሶታ ግዛት፣ ሚኒያፖሊስ ከተማ በነጭ ፖሊስ ታንቆ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ ፎቶ የሚያሳየው ቲሸርት እየቸረቸረ የነበረው አማዞን የኢንተርኔት መገበያያ ለጊዜው ያን ልብስ መሸጥ ማቆሙን አስታወቀ።
"በመደብሮቼ እንዲያ ዓይነት ልብስ መሸጥ ትቻለሁ" ብሏል ትልቁ ገበያ አማዞን።
ቲሸርቱ በ15 ዶላር እየተቸበቸበ ነበር። ልብሱን ያቀርብ የነበረው ደግሞ ሌላ ሦስተኛ ወገን መሆኑ ታውቋል።
ስለጉዳዩ ተጠይቆ ለቢቢሲ በደብዳቤ ምላሽ የሰጠው አማዞን ይህንን ልብስ አማዞን ገበያ ላይ ያስቀመጠው ወገን ማንነት እየተጣራ ነው።
የኢንተርኔት ገበያ መመሪያው ማንኛውንም እቃ በአማዞን በኩል መሸጥ ያሰበ ነጋዴ ምርቶቹ ወንጀልና የወንጀል ሂደትን የማያመላክቱ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
ለቢቢሲ ይህ ዕቃ ገበያ ላይ መሆኑን የጠቆመው አንድ የአማዞን ሠራተኛ ነው።
ምንም እንኳ አሁን ይህ ቲሸርት በኦንላይን ገበያ የማይገኝ ቢሆንም ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ኮፍያዎችና ቲሸርቶች በኢንተርኔት መደብሩ ይታያሉ።
ከግርጌያቸው የተጻፈባቸው መልዕክት ግን የነጭ ፖሊሶችን ተመጣጣኝ ያልሆነ ጉልበት መጠቀምን የሚያወግዙ መልዕክቶች ናቸው።
ሆኖም እነዚህ ምርቶች ከመደብሩ ተሸጠው ስለማለቃቸው የሚገልጽ ጽሁፍ ሰፍሮባቸዋል።
አማዞን ከዚሁ ክስተት ጋር ተያይዞ ለቀረበለት ጥያቄ ለቢቢሲ በላከው የጽሑፍ ምላሽ ምርቶቻቸውን በአማዞን በኩል የሚሸጡ ሁሉም ነጋዴዎች ያስቀመጥናቸውን መመሪያዎች መከተል ይገባቸዋል። ይህን በማያደርጉት ላይ ከንግድ ሰንሰለቱ እስከመባረር የሚደርስ እርምጃ እንወስድባቸዋለን ብሏል።
አሁን ተገቢነቱ እያነጋገረ ያለው ቲሸርትም ከኢንተርኔት ገበያው ሙሉ በሙሉ ተወግዷል።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በደማቅ ሁኔታ የተፈጸመለት ሟቹ ጆርጅ ፍሎይድ የተገደለበት መንገድ በመላው አሜሪካ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።












