በኮሮናቫይረስ ሰበብ ትኩረት የተነፈጉት የዓለማችን ገዳይ ችግሮች

ጊኒ ውስጥ፤ የሁለት ዓመቱ ኤሚሊ ኦሞኑዎ ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝ የተቦረቦረ ዛፍ ውስጥ ገብቶ መጫወት ያዘወትራል። ዛፉ የሌሊት ወፎች መኖሪያ ነው።

የአካባቢው ታዳጊዎች የሌሊት ወፎቹን ጠብሶ የመብላት ልማድ አዳብረው ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን ኤሚሊ በጠና ታመመ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2013 ላይ እሱ ብቻ ሳይሆን እናቱ፣ እህቱና አያቱ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ተያዙ። ሕይወታቸውም ተቀጠፈ።

ከቀብራቸው በኋላ በሽታው ይስፋፋ ጀመር። ይህ በተከሰተ በዓመቱ 49 ሰዎች በበሽታው ተይዘው፣ 29 ሰዎች ሞቱ። ተመራማሪዎች በሽታው ኢቦላ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት በበሽታው ሳቢያ በዓለም ከ11,325 በላይ ሰዎች ሞተዋል። የወቅቱ የዓለም ጭንቅ ይህ በሽታ ብቻ አልነበረም።

በሽታው የጤና ሥርዓትን አቃውሷል። ሠራተኞች ሞተዋል። ብዙ ሆስፒታሎች ተዘግተዋል። ክፍት የነበሩትም ከአቅማቸው በላይ ህሙማን እያስተናገዱ ነበር።

በበሽታው ክፉኛ በተጠቁት ሴራሊዮን፣ ላይቤርያ እና ጊኒ ውስጥ ሰዎች ወደ ህክምና መስጫ መሄድ አቁመው ነበር። በሽታው አስፈርቷቸው ነበር። በሽታውን ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችንም ፈርተዋቸው ነበር።

ባለሙያዎቹን ማንም ሊጠጋቸው አልደፈረም። 2017 ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳው፤ በወረርሽኙ ምክንያት ለህክምና ሙያ የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል።

ሐኪም ቤት መውለድ የሚፈልጉ ነፍሰ ጡሮች ቁጥር 80 በመቶ ቀንሷል። ወባ የያዛቸው ልጆችን ወደ ሆስፒታል የሚወስዱ ቤተሰቦች ደግሞ 40 በመቶ አሽቆልቁሏል። ለክትባት ወደ ጤና ተቋም የሚሄድ ሰውም ዝቅ ብሎ ነበር።

በዓለም አቀፍ ርብርብ ወረርሽኙ ቢገታም፤ ከበሽታው በላይ ጉዳት ያስከተሉት ከወረርሽኙ ጋር ተያይዘው የመጡ ችግሮች ነበሩ።

ከዘንድሮው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም መሰል ስጋት አለ።

ሌሎች በሽታዎች ችላ መባል

አገራት ኮቪድ-19ኝን መዋጋት ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተናግረዋል። ለህሙማን አልጋ፣ ቬንትሌተርም ተዘጋጅቷል። በተለያየ ዘርፍ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ወደመከላከል ተዘዋውረዋል።

የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የአዕምሮ ጤና፣ ካንሰር እንዲሁም መደበኛ የህክምና ክትትሎችም ችላ ተብለዋል። በመላው ዓለም ያሉ የካንሰር ህሙማን፣ የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው፣ አስቸኳይ ቀዶ ህክምና የሚሹ ሰዎችም ሰሚ አጥተናል እያሉ ነው።

በባልካን አገራት ውስጥ አደገኛ በሆነ ቦታ ለማስወረድ የተገደዱ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ለራሳቸው የጥርስ ህክምና ለመስጠት ከመሞከር ውጪ አማራጭ ያጡም አሉ። ለወባ ህክምና የሚውለው ሀይድሮክሎሮኪን በብዛት ያከማቹም አልታጡም።

በተለይ በድሀ አገራት ከወረርሽኙ አኩል ኤችአይቪ፣ ቲቢና ወባ ያሰጋሉ። ሌላው ችግር በተገቢው ጊዜ ክትባት አለማግኘት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ወረርሽኙ ቢያንስ የ68 አገሮችን የጤና ዘርፍ ስለሚያቃውስ፤ 80 ሚሊዮን ጨቅላዎች ክትባት ባለማግኘት ለኩፍኝ፣ ፖሊዮና ሌሎችም በሽታዎች ይጋለጣሉ።

በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠፋው ፖሊዮ ዳግመኛ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።

የዓለም አቀፉ የምግብ ተቋም ዋና ኃላፊ ዴቪድ ቢስሊ፤ ዓለም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው አይነት ቸነፈር ይጠብቃታል። 130 ሚሊዮን ሰዎች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው። አሁን ላይ 135 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል።

በእንቅርት ላይ. . . እንዲሉ አገራት እንቅስቃሴ መገደባቸውም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የሚፈጠረው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ አልያም ጠጪ እንዲሆኑም ሊገፋፋ ይችላል።

የኮቪድ-19 ጉዳት ምን ያህል ጥልቅ ነው?

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲው የበሽታዎች ጥናት ባለሙያ የሆኑት ኢፒዲሞሎጂስቱ ቲሞቲ ሮበርተን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ወረርሽኙ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ተወያይተዋል።

“በ2014 በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላ ሲቀሰቀስ ምን እንደተፈጠረ ስላየን አሁንም ምን እንደሚከሰት አውቀናል” ይላሉ።

ኮቪድ-19 ከሰሀራ በታች ባሉ ድሀ አገሮች በዋነኛነት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት የነቲሞቲን ትኩረት አግኝቷል። ሁለት ጉልህ ነጥቦችም አስቀምጠዋል።

አንደኛው በጤና ሥርዓት ላይ የሚፈጠረው ቀውስ ነው። “ሰዎች እርዳታ ለመጠየቅ ሊፈሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎች ሊታመሙ፣ ሙሉ ትኩረታቸውን ወረርሽኙ ላይ ሊያደርጉ፣ የመድኃኒት እጥረት ሊገጥማቸውም ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።

ሁለተኛው ችግር በቂ ምግብ ባለማግኘት ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ ነው።

በተመራማሪዎች ትንበያ መሠረት፤ የጤና አገልግሎት የማግኘት እድል 50 በመቶ ሲቀንስ፤ ምግብ ማጣት ደግሞ በዚያው መጠን ይጨምራል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ልጆች፣ 56,700 እናቶች ሊሞቱ ይችላሉ።

የልጆች ሞት ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል ኒሞንያ [የሳንባ ምጭ] እና በተቅማጥ ሳቢያ የሚከሰት የፈሳሽ እጥረት ይጠቀሳሉ። ሴቶች ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሕይወታቸው ሊያልፍም ይችላል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በየቀኑ ለ100 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ እያደለ ሲሆን፤ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉት ሕይወታቸው የተመረኮዘው በዚህ እርዳታ ላይ ነው።

በተቋሙ አሃዝ መሠረት፤ እርዳታው ከተቋረጠ፤ በቀጣይ ወራት በየቀኑ 300 ሺህ ሰዎች በረሀብ ሊሞቱ ይችላሉ።

የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄን ሀዋርድ እንደምትለው፤ በመላው ዓለም የተራቡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ተችሎ ነበር። ባለፉት አምስት ዓመታት በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ይህ ለውጥ ተቀልብሷል።

“ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ክፉኛ ለረሀብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አስደንግጦን ነበር” ትላለች።

ወረርሽኙ 130 ሚሊዮን ሰዎችን ብቻ አይደለም ምግብ የሚያሳጣው። ድርጅቱ እርዳታ እንዳይሰበስብም እንቅፋት ይሆናል።

ጄን እንደምትለው፤ የምግብ እጥረት የከተማ ነዋሪዎችም ችግር ነው። የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በዋነኛነት በወረርሽኙ ይጠቃሉ።

“ገጠር የአትክልት እርሻ፣ ወይም ላም ያላት አክስት ያለው ሰው አለ። በመጠኑም ቢሆን ድጋፍ ይገኛል። ከተማ ውስጥ ግን ከመደብር ውጪ መሄጃ የለም” ስትል ታስረዳለች።

የጉልበት ሠራተኞች፣ የግንባታ ሠራተኞችና ሹፌሮች ደግሞ በቀዳሚነት ተጋላጭ ናቸው።

ከቫይረሱ በላይ ምን ይገድላል?

ኮቪድ-19 አረጋውያንን በይበልጥ ይጎዳል። ከኒው ዮርክ በተገኘ መረጃ መሠረት፤ 75 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ከ811 ጊዜ በላይ በወረርሽኙ ሞተዋል። ይህም ወደ 17 ዓመት ገደማ ካሉ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸሩ ነው።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች አብዛኛው ዜጎቻቸው ወጣቶች ናቸው።

ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር የሕዝቡ አማካይ እድሜ 15.2 ነው። በበሽታው እስካሁን የሞቱት 254 ሰዎች ናቸው። በተቃራኒው በጣልያን አማካይ እድሜ 45 ነው። በበሽታው የሞቱ ሰዎች 33,000 ደርሰዋል።

በእርግጥ ከሞቱት ሰዎች መካከል ምን ያህሉ በወርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጡ? የሚለው አከራካሪ ነው። ምክንያቱም አረጋውያን የሚጋለጡት ለኮቪድ-19 ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወቅት ጠብቀው ለሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ህመሞችም ነው።

በኮሮናቫይረስ በቀጥታ ባይሞቱም በተዘዋዋሪ ለህልፈት የሚጋለጡት ያደጉ አገራት ነዋሪዎች ጭምርም ናቸው። ለምሳሌ ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም የሚደረገው ጥረት ቀንሷል።

በዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ማዕከል ዳይሬክተር ሣራ ሂሎም፤ “ካንሰር ጊዜ አይሰጥም። በሽታው ቶሎ ከተገኘ ለማከምም ይቀላል” ይላሉ።

ሆኖም ግን አገሪቱ እንቅስቃሴን ስትገታ የካንሰር ምርመራ ቆሟል። ያ ማለት ደግሞ ቀድሞ በየወሩ ይገኙ የነበሩት 1,600 የካንሰር ህሙማን አሁን ግን በሽታቸው አይታወቅላቸውም ማለት ነው።

ህሙማን ከቤታቸው እየወጡ ስላልሆነ መደበኛ ምርመራ ማቆማቸው ሌላው ስጋት ነው። አንድ የካንሰር ሐኪም እንደሚሉት፤ ሕክምና በመጓተቱ ሳቢያ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ወደ 60 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ።

ሌላው የዚህ ወረርሽኝ ጉዳት የሚያስከትለው የምጣኔ ሀብት መላሸቅ ነው። ለዚህም ጀርመንን መጥቀስ ይቻላል። በዋናነት ድጎማ ላይ የሚመሠረቱ የካንሰር ጥናቶች አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውም አይቀሬ ነው።

ሣራ፤ የካንሰር ምርመራና ሕክምና በአፋጣኝ መጀመር አለበት ትላለች።

የዓለም ምግብ ፕሮግራሟ ጄን ደግሞ አገራት ለዜጎቻቸው የአደጋ ጊዜ መዘጋጃ የሚያደርጉበትን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ትናገራለች። አንደኛው መንገድ ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ታዳጊዎችን መመገብ መቀጠል ነው። የንግድ ሰንሰለት እንዳይበጣጠስ ጥረት መደረግ እንዳለበትም ትመክራለች።