ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም የሚለው ጥሪ ተቀባይነት የለውም፡ የኦሮሚያ ክልል

የፎቶው ባለመብት, Oromia Communication Bureau
ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም በማለት ብጥብጥ ለማንሳት መንቀሳቀስ ተቀባይነት የለውም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ገለጸ።
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት "ወረርሽኝ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሕዝብን ለተቃውሞ መጥራትና ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም በማለት ብጥብጥ ለማንሳት የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።
"የመንግሥት ስልጣንን ከምርጫ ውጪ በአቋራጭ ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ ማስታወስ እንፈልጋለን" ብለዋል የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ።
የክልሉ መንግሥት ከምን ጊዜውም በላይ የሕዝቡን ሠላምና ጤና ለመጠበቅ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ "እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ለመያዝ ሲሉ ሰው ቢሞት ለእነሱ ምንም ማለት አይደለም። የሞት ጥሪ ለሕዝቡ እያደረጉ ነው" በማለት "ይህ ትልቅ ስህተት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል" ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ በሽታ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሰዎችን ለተቃውሞ ሰልፍ ወደ አደባባይ መጥራት ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው ሲሉ አሳስበዋል።
"የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ መንግሥት እና የጤና ባለሙያዎች የዜጎችን ህይወት ለመታገድ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ሰዎችን ለተቃውሞ ስልፍ አደባባይ የሚጠሩ አካላት ስልጣንን በአቋራጭ መያዝ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው" ብለዋል።
አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ ላይ መሳሪያ በመተኮስ፣ የመንግሥት ባለስልጣናትን በመግደል፣ በማስፈራራት እና የታችኛው የመንግሥት መዋቅርን በመናድ የሚገኝ ሰልጣን የለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጨምረውም "ለ27 ዓመታት ይህችን አገር ዘረፈው፤ ይህም አልበቃ ብሏቸው በመቀሌ መሽገው ተቀምጠው አገሪቷ ሰላም የሚነሱ" ያሏቸው ወገኖች የክልሉ ሠላም ለማደፍረስ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሲያብራሩም "ኦሮሚያ የግጭት ሜዳ ለማድረግ፣ 'ኦሮሚያ ካልተረበሸች ኢትዮጵያ መረበሽ አንችልም' የሚል ስልት ቀይሰው፤ በኦሮሚያም ግጭት እንዲፈጠር ድጋፍ የሚያርጉ፣ እና የእነሱ ተላላኪዎች ይህ አካሄድ የሚያዛልቃቸው ባለመሆኑ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት ጥሪ ያቀርብላቸዋል" ብለዋል።
ከዚህ በዘለለ በክልሉ ሁከት ለመፍጠር እየሰሩ ናቸው ያሏቸውን፣ የተቃውሞ ሰልፍ እየጠሩ ነው ብለው ያነሷቸውንና ከመስከረም በኋላ መንግሥት የለም ብለዋል ያሏቸውን ወገኖች በስም አልጠቀሱም።












