በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች ሥራ ሊያጡ እና የአገር ውስጥ ምርት እድገት 11.2 በመቶ ሊቀንስ ይችላል

ብር የሚቆጥር ሰው
የምስሉ መግለጫ, የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ ነው

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከበድ ያለ ነው። ግዙፍ የምጣኔ ሃብት አላቸው የሚባሉት እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንገድደም እና ሕንድ ባሉ አገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ቫይረሱ ባመጣው ሰበብ ሥራ ፈላጊ ሆነዋል።

ወረርሽኙ በአገራችንም ምጣኔ ሃብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ወረርሽኙ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖ ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጥናት ሠርተዋል።

የፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጥናት እንዳሳየው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት 5.6 በመቶ ሊጎዳው እንደሚችል ይጠቁማል።

የአገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) በአማካይ 11.2 በመቶ ሊላሽቅ ይችላል

"ልክ አውሮፓ እና አሜሪካ እንደተስፋፋው፤ ቫይረሱን እኛም አገር ቢሰራጭ ኢኮኖሚያችን እሱን የሚሸከምበት አቅም የለውም። ከሚጠበቀው በላይ ነው የሚጎዳን። ምክንያቱም እነሱ [ምዕራባውያን አገራት] የተሻለ ኢኮኖሚ፣ የሰው ኃይል እና ቁጠባ አላቸው። እኔ ባሰላሁት መሠረት ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ እጅግ ትልቅ ነው" ይላሉ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ አለማየሁ ገዳ።

የፕሮፌሰሩ ጥናት እንደጠቆመው ኢትዮጵያ በ2020 (በአውሮፓውያን አቆጣጠር) የበጀት ዓመት የአገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) በአማካይ 11.2 በመቶ ሊላሽቅ ይችላል። ፕሮፌሰር አለማየሁ እንደሚሉት ከሆነ፤ ከሐምሌ 2012 እስከ ሰኔ 2013 በሚዘልቀው የበጀት ዓመት ላይ ቫይረሱ የሚያስከትለው ጉዳት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሚገታ ከሆነ፤ የአገር ውስጥ ምርት እድገቱ ሊቀንስ የሚችለው በ5.6 በመቶ ነው። ቫይረሱ የሚስከትለው ጉዳት ግን እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት የሚዘልቅ ከሆነ የአገር ውስጥ ምርት እድገቱ የሚቀንሰው በ16.7 በመቶ ይሆናል።

ፕሮፌሰሩ የቫይረሱ ስርጭት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ድቀት ለመቀነስ "ያለ ኃይልን በማሰባሰብ ቫይረሱ ወደ ህብረተሰቡ ከመሰራጨቱ በፊት በቁጥጥር ሥር ማድረግ ነው" ሲሉ ይመክራሉ።

ከውጪ የሚላክ ገንዘብ መቀነስ

ፕሮፌሰር አለማየሁ ዘመዶቻችን ከውጪ በባንክ በኩል የሚልኩት ገንዘብ አገሪቱ ምርት ወደ ውጪ ልካ ከምታገኘው ዶላር በላይ መሆኑን ይናገራሉ።

"የመንግሥት አሃዞችን ብንመለከት እንኳ፣ አገሪቱ ወደ ውጪ አገራት ምርት ልካ የምታገኘው ገቢ 2.8 እስከ 3 ቢሊዮን ነው። እንደውም ወደ ውጪ የሚላከው ምርት እየቀነሰ ነው። ከውጪ የሚላከው ገንዘብ ግን ከ4.5 እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ነው" ይላሉ።

"መንግሥት ወደ ውጪ እንደሚላኩ ምርቶች ሁሉ ከውጪ ወደ አገር በሚላክ ገንዘብ ላይ በቂ አትኩሮት አይሰጥም የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ "ምርት ወደ ውጪ ልከን የምንሸጠው 3 ቢሊዮን ነው። የምናስገባው ደግሞ 17-18 ቢሊዮን ዶላር ነው" በማለት ይሄን የንግድ ክፍተት ለመሸፈን 'ሬሚታንሱ' ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት ይናገራሉ።

በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ይልኩ የነበሩ ሰዎች እንደ ከዚህ ቀደም መላክ ባለመቻላቸው አገሪቱ ከ'ሬሚታንስ' ወይም ከውጪ ይላክ ከነበረ ዶላር ታገኝ ነበረውን ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል ይላሉ። ዓለም አቀፍ ትንበያዎች ከሃብታም አገራት ወደ ትውልድ አገራት የሚላክ ገንዘብ መጠን በ26 በመቶ እንደሚቀንስ ማሳየታቸውን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ይናገራሉ።

ሥራ አጥነት

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአሜሪካ እና አውሮፓ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ሥራ አጥ አድርጎ የመንግሥት ድጎማን እንዲጠብቁ አስገድዷል።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳም፤ በአገራችንም ኮቪድ-19 ቢያንስ እስከ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አጥ ሊያደርግ እንደሚችል በጥናታቸው አመላክተዋል። "1.8 ሚሊዮን ሰው የመንግሥት ሰራተኛ ነው። የመንግሥት ሰራተኛው በወረርሽኙ ሳብያ ከሥራው ይፈናቀላል ብለን አንጠብቅም" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ "የግል ሴክተሩ ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን ቀጥሯል። ከእነዚህም መካከል ግማሽ ያክሉ ሥራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ" ይላሉ።

ከእነዚህ በተጨማሪ "ራሱን ቀጥሮ የሚያሳድር ደግሞ 3.1 ሚሊዮን አለ። እነዚህም ተጋላጭ ናቸው። ሥራቸውን በቀላሉ ሊያጡ ይችላሉ" ይላሉ።

በአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ውሰጥ የሚታዩ ሰዎችና የምግብ ምርቶች
የምስሉ መግለጫ, በምግብ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መጨመር

መፍትሄ

"የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ብዙ አይጎዳም። ብዙ የሚጎዱት የአገልግሎት እና ኢንደስትሪ ዘረፎች ናቸው። ስለዚህ ያለ የሌለ አቅማችንን በእርሻው ላይ ማድረግ አለብን። ግብርናው የሚወድቀውን ኢኮኖሚያችንን ሊታደግልን ይችላል" በማለት እንደመፍትሄ ካስቀመጧቸው የመጀመሪያውን ነጥብ ያነሳሉ። ለዚህም በሽታው ወደ ገጠር እንዳይገባ ጥንቃቄ መድረግ እንዳለበት ፕሮፌሰር አለማየሁ ያሳስባሉ።

መንግሥት ከግል ሴክተሩ ጋር በመነጋገር ሊታገዙ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ።

ፕሮፌሰር አለማየሁ እንደሚሉት በቫይረሱ ስርጭት እጅጉን ከሚጎዱት መካከል ራሳቸውን ቀጥረው የሚገኙት 3.1 ሚሊዮን ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ናቸው በማለት "ሥራ በሌለበት የሥራ ቦታ እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ እየከፈሉ ነው። መንግሥት እያለ ያለው 'እባካችሁ ቤት ኪራይ ቀንሱላቸው' ነው። እንደዛ ብቻ መሆን የለበትም። መንግሥት የቤት ኪራይ የማይከፍሉበትን መንገድ ቢፈልግ እና ለአከራዮች ደግሞ እንደ ቼክ ወይም ቦንድ ባሉ ሰነዶች ማረጋገጫ ቢሰጥ ይረዳል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

የግል ዘርፉም ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት እንዳለበትም ሃሳባቸውን ኣቀርባሉ።