ናይጄሪያ ምግብ ከውጪ ለማስገባት ገንዘብ የለኝም አለች

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው ችግር የተነሳ አገራቸው ምግብ ከውጪ ለማስገባት "ገንዘብ የላትም" አሉ።

በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ ቀድማ የመጀመሪያውን የሆነችው ናይጄሪያ የውጪ ምንዛሪ ችግር ስላጋጠማት የአገሪቱ አርሶ አደሮች ሕዝቡን መቀልብ የሚችል መጠን ያለው ምግብ እንዲያመርቱ ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል።

ቡሐሪ ይህንን የተናገሩት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሚከሰትን የምግብ ዋስትና ችግር በተመለከተ ስጋቶች በመፈጠራቸውና በአገሪቱም በምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ተከትሎ ነው።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት የአገሪቱ አርሶ አደሮች እንኳን በዚህ በወረርሽኙ ወቅት ይቅርና ከዚያ በፊትም 200 ሚሊዮን የሚደርሰውን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ማሟላት አይችሉም ነበር።

ምንም እንኳን የናይጄሪያ የግብርና ዘርፍ በርካታ ሰዎች የተሰማሩበት ዋነኛ መስክ ቢሆንም፤ ከነዳጅ ዘይት በሚገኝ ገቢ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ በሆነው የአገሪቱ መዕተዓኘየ ሐዓዕጠዕ ተነሳ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል።

ናይጄሪያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በድንበሮቿ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ከታይላንድ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባውን የሩዝ ምርት በመግታት በአገር ውስጥ ለሚመረተውን ሩዝ ገበያ ለማመቻቸት ጥረት ስታደርግ ነበር።

ናይጄሪያ ከውጪ የሚመጣ የሩዝ ምርት ላይ ክልከላ ከመጣሏ ቀደም ብሎ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊየን ቶን በላይ ሩዝ ከታይላንድ ታስገባ ነበር።

አገሪቱን በሚያዋስኗት አገራት ድንበር በኩል የሚገባው ሩዝ የተከለከለ በመሆኑ በወደብ በኩል ብቻ ነው ሩዝ ወደ ናይጄሪያ እየገባ ያለው። በዚህም ላይ ከፍተኛ ግብር በመጣሉ ዋጋውን አስወድዶታል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ በኋላ ናይጄሪያ ውስጥ የምግብ ዋጋ ላይ ጭማሪ የተከሰተ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዘይት ዋዳ በመውደቁ ምክንያት ደግሞ መንግሥት ያገኘው የነበረው በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እንደተነበየው በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ናይጄሪያ በዚህ ዓመት ኢኮኖሚዋ በ1.5 በመቶ ያሽቆለቁላል።