ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ያወጣቸው የቤተልሔም አበበ ገፀ ባህሪያት
ቤትልሔም አበበ 'ማኒ ሃይስት' በመባል በሚታወቀው የኔትፍሊክስ ተከታታይ ፊልም ላይ ተዋናዮቹ የሚለብሱትን፣ የስፓኒሽ አርቲስቱን የሳለቫዶር ዳሊን ማስክ በመሆን፣ ሲያምራት የ'ፓይረትስ ኦፍ ዘ ካሪቢየን' ዋና ገፀ ባህሪ ካፕቴን ጃክ ስፓሮውን፣ ሲያሰኛት ደግሞ 'ዘ ማስክ' የተባለውን በፈርንጆቹ በ1994 የወጣው ፊልም ላይ ያለውን ገፀ ባህሪ በመምሰል ራሷን ትቀያይራለች።
ይህ ብቻ ግን አይደለም፤ ሌሎች ብዙ ገፀ ባህሪያትን በመሆን ዘመድ ጓደኞቿን ታዝናናለች። ከቤቢ ዮዳ (ስታር ዎርስ ፊልም እ.አ.አ 2019)፣ ከማሌፊሸንት (ማሌፊሸንት 1 እና 2 ፊልም እ.አ.አ 2014ና 2019 ) እና ከካፕቴን ስፖክ (ስታር ትሬክ ፊልም እ.አ.አ 1966) ገፀ ባህሪያት በስተጀርባ ያለችው ቤተልሔም አበበ ማን ናት?
ቤተልሔም ከአዲስ አበባ ሕንፃ ኮሌጅ የዛሬ ሦስት ዓመት ተመረቃለች። "ሁሌም ለጥበብ ታደላ ነበረ" የምትለው ልቧም፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከማቅናቷ በፊት አልማው እንደነበረው ወደ ጥበብ ጎዳና መራት። የሥነ-ሕንፃ ምሩቅ የሆነችው ቤተልሔም በሁለቱ ሥራዎች መካከል ብዙም ልዩነት የለውም እያለች ቀስ በቀስ ወደ ሜካፕ [የገጽ የቅብ ባለሙያ] ሥራ ተሰማራች።
ሆኖም ግን እሷ የምትሠራው በውበት ሳሎን ወይም ለሠርግ እንደሚሞሽሩት፣ በሃገራችን የተለመደው ሜካፕ [የገጽ ቅብ] አልነበረም። የቤቲ ሜካፕ ሥራ አንዳንዴ ሊያስፈራ የሚችል፣ አንዳንዱን ግር የሚያስብል ወይንም አልፎ አልፎ የሚያዝናና እና 'ወይ ጉድ' ሊያስብል የሚችል ነው።
"በእርግጥም የጀመርኩት ብዙዎቻችን በምናውቀው በኮስሜቲክ ወይም ማስዋብያ ሜካፕ ነው" የምትለው ቤትልሔም፣ ገና ሳትመረቅ የሚወዷት አክስቷ ከውጪ አገር ለሠርግ መጥተው ለሜካፕ ሥራ ያላትን ተሰጥዖ ልብ አሉ። ወደ ኑሮዋቸው ሲመለሱ "ቢያስፈልግሽ" ብለው የተሟላ የሜካፕ ዕቃ ይልኩላታል። ከዚያም በተላከላት ስጦታ የገጽ ቅቡን ሥራ ተያያዘችው።
ቤቲ ግን ትፈልግ የነበረው ፊልም ላይ የምታያቸውን ከሰው አንስቶ አውሬ እስከሚምስሉ ያሉትን ገፀ ባህሪያት አስመስሎ መሥራት ነበር።
ከተመረቀችም በኋላ የፕሮዳክሽን ድርጅት ተቀላቅላ የመጀመሪያዋን ሥራ፣ አርት ዳይሬክተር ሆና የፊልም አልባሳትና የቀረፃ መድረኮችን ዲዛይን በማድረግ ጀመረች። ቤትልሔም የሚታዩ ጥበባትን እንደምትወድ በመግለፅ "ፊልም ላይ ሴት ወይም ኢንቫይሮንመንት ዲዛይን በጣም እወዳለሁ። ገፀ ባህሪያቱ ምን ይምሰሉ፣ ምን ይልበሱ፣ የት ይሁኑ እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ልዩ የሆኑ 'ክሪዬቲቭ' መፍትሔዎችን ማግኘት ያስደስተኛል" ትላለች።
ከልጅነቷ የሚያስታውሷት ጓደኞቿ መቀባባት፣ መለባብስ እንደምትወድ ያስታውሳሉ የምትለው ቤቲ "ለቀልድ እንጂ" ሥራ ብላ እንዳልያዘቸው ታስረዳለች። የሚወዷት አክስቷ ግን በየጊዜው የጨረሰቻቸውን የሜካፕ ዕቃዎችና ሌላም ሌላም ጨመር ጨመር እያደረጉ መላካቸውን አላቆሙም።
ሁሉም ነገር የጀመረው በምዕራቡ ዓለም የሙታን ቀን ተብሎ በሚከበርበት ዕለት (ኦክቶበር 31፡ 2019)ነው።
'ለኮስትዩም ፓርቲ' የተጠራችው ቤቲ ራሷን ቀያይራ 'ባትማን' በተሰኘው ፊልማ ላይ ክፉ ገፀ ባህሪ የሆነውን 'ዘ ጆከር'ን ሆና ተገኘች። በዚያ ዝግጅት ላይ ያዩዋት በሙሉ በሥራዋ በጣም መደነቃቸውን ይገልፁላታል። የሰዎችን አድናቆትና አበርታች ስሜቶችን ልብ ያለችው ቤተልሔም ተሰጥዖ እንዳላት ተረዳች።
"ጆከርን ከሠራሁ በኋላ ብዙ ልሠራቸው የምችላቸውን ገፀ ባህሪያት ዘረዘርኩኝ። ልሠራቸውም አቀድኩኝ። እንደውም የራሴን ስቱድዮ ከፍቼ ሁሉ እውን ላደርጋችው ተመኘሁኝ" የምትለው ቤተልሔም ፍላጎቷ እያደር እያደገ ቢመጣም እንኳ በዕለት ተዕለት ሩጫ መካከል እምብዛም ጊዜ አለማግኝቷን ትናገራለች።
ከወራት በኋላ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ ዓለምን ሲያንቀጠቅጥና ሁሉም ከቤት ሆኖ እንዲሠራ ሲታዘዝ ተመኝታ የነበረውን ጊዜ ማግኘቷን ትናገራለች። ከዚያም ከዚህ ቀደም የተዘረዘሩትንና ማይክል ጃክሰን ድሮና ዝንድሮ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ከእነ ባለቤታቸው ዝናሽ ታያቸው፣ ጃንሆይንና ሌሎችንም ትሠራ ጀመር።
ከሥነ-ሕንፃ ትምህርት ተነስታ ወደ የገጽ ቅብ፣ ለዚያውም ወዳልተለመደው፣ ማቅናቷን ሲሰሙ ቤተስቦቿ ምን እንዳሉ ጠየቅናት።
"ወላጆቼ በጣም ደስተኛ ናቸው። በጣም ያበረታቱኛል። መጀመሪያ በግዳጅ ሳይሆን የወላጅ ሃሳባቸውን፣ ሕክምና እንዳጠና ይፈልጉ ነበር። እኔ ግን አርት እወድ ስለነበር ሥነ-ሕንፃን መረጥኩኝ። ምክንያቱም 'አርኪቴክቸር' ዲዛይንም አርትም ጥበብም ነው" ትላለች። አክላም "ሥነ-ሕንፃ ስገባም ሆነ ከዚያም ወደ ሜካፑ ስሰማራ በጣም 'ሰፖርት' ያደርጉኝ ነበር። ዕድለኛ ነኝ" በማለት ለቤተሰቦቿ ያላትን አድናቆት ትገልፃለች።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት በጅማ ዩኒቨርሲቲ 4ኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ታናሽ እህቷም ቤት በመሆኗ አልፎ አልፎ እንደምታግዛት አጫውተናለች። "ታናሽ እህቴ እንደውም እኔን ለማገዝ ስትል ሌሊት እንኳን ትነሳልኛለች" የምትለው ቤቲ ፀጥታው ለሥራ ስለሚመቻት ሌሊቱን ቀን፣ ራቷን ቁርስ አድርጋ ሠርታ አድራ ሲነጋጋ እንደምትተኛ ትናገራለች።
"ጠዋት ያለው የተፈጥሮ ብርሃን ለፎቶ በጣም ይመቻል። ስለዚህ ሌሊት የሠራሁትን ፎቶ እንድታነሳኝ እህቴን ብዙ ጊዜ እቀሰቅሳታልሁ። እርሷም ትታዘዘኛለች። አንዳንዴ እንደውም እሷ ከእኔ ጠየም ስለምትል ወደ አንዳንድ ገፀ ባህሪያት እሷንም ጭምር እቀይራታለሁ" በማለት የሥራ ሂድቷን ታስረዳለች።
"አንዳንዴ ክፉ ነገር ሲገጥመን ጥሩ ጎኑን ፈልገን ራሳችንን ወደሚጠቅመን ነገር መቀየር ሃሪፍ ነው" በማለት ምንም ነገር ወይም ማንም ሰው እንዳሰበው ነገሮች እንደማይሳኩ ትናገራለች። የፈለገቻቸውን ገፀ ባህሪያት ለመሥራት በአሁን ሰዓት ከበድ እንደሚል የምትናገረው ቤትልሔም ያሰበቻቸውን 35 ገፀ ባህሪያት ለመሥራት የሚያሰፈልጋት ዕቃ እጇ ላይ አለመኖሩን ትናገራለች።
ሆኖም ግን እስከዛሬ አክስቷ የላኩላትን የኮስሞቲክስ ሜካፕ በመጠቀም፣ ከ35ቱ አሥሩን ገፀ ባህሪያት ባለፉት 4 ሳምንታት ብቻ መሥራቷን ትናገራለች።
"እንደ ልቤ ወጥቼ የምፈልገውን ዕቃ ባሁን ሰዓት ማሟላት አልችልም። ቢሆንም ግን መሥራት የምፈልጋቸውን ሳይሆን ባሉኝ ዕቃዎች መሠረት መሥራት የምችላቸውን ነው እየሠራሁ ያለሁት። ለምሳሌ ጃክ ስፓሮውን ለመሥራት ፊልሙን ደግሜ ማየት ሁሉ ነበረብኝ፤ ምክንያቱም ሁሉን ነገር ማመሳሰል የምችልበትን ዕቃ ማሰብ ነበረብኝ። ማንኛውንም ገፀ ባህሪ ከመሥራቴ በፊት ቅድመ ጥናት አደርጋለሁ" የምትለን ቤቲ እንደ ገፀ ባህሪያቱ መልበስና መምሰል ብቻ ሳይሆን ገፀ ባህሪውን መላበስ አስፈላጊ መሆኑን ትገልፃለች።