ሳኡዲ አረቢያ በተወሰኑ ጥፋተኞች ላይ የሞት ቅጣትን ልታስቀር ነው

ሳኡዲ አረቢያ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ታዳጊዎችን በሞት መቅጣት ልታቆም እንደሆነ የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ንጉሥ ሰልማን ያረቀቁት ነው የተባለው ይህ ሕግ አገሪቱ ግርፋትን እንደ ወንጀል መቀጣጫ ማድረግ አቆማለሁ ካለች ጥቂት ቀናት በኋላ ነው የታወጀው።

ሳኡዲ ፊርማዋን ያኖረችበት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ጉባዔ ሕፃናት ለሚፈፅሙት ቅጣት የሞት ፍርድ ሊፈርድባቸው አይገባም ይላል።

የመብት ተማጋቾች ሳኡዲ አረቢያ የሰው ልጅ መብትን ክፉኛ እየረገጠች ነው ሲሉ ይኮንናሉ።

ሐሳብን በነፃነት መግለፅ የታፈነው ነው የሚሉት ተሟጋቾቹ መንግሥትን መቃወም ያለ ሕግ አግባብ ሊያሳስር ይችላል ሲሉ የሳኡዲን አገዛዝ ይተቻሉ።

ባለፈው ዓመት በሳኡዲ 184 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች። ይህም እስከዛሬ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው፤ ይላል አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ቡድን።

ከእነዚህ መካከል አንድ ግለሰብ ከ18 ዓመት በታች እያለ በፈፀመው ጥፋት ነው በሞት የተቀጣው ሲል ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል።

እሁድ የወጣው የሳዑዲ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኝ መግለጫ እንደሚያመለክተው ንጉሡ ዕድሜያቸው ለጋ የሆኑ ሰዎች ለፈፀሙት ቅጣት የሚሰጠው ሞት ፍርድ ተሽሮ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እሥር እንዲቀጡ ይሁን ብለዋል።

የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት አዋድ አላዋድ እንዳሉት አጥፊዎች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች የሚታረሙበት እሥር ቤት ይገባሉ።

''ትዕዛዙ ወደ ዘመናዊ የወንጀል ቅጣት ዘዴ እንድመጣ ያግዘናል'' ሲሉ የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት አዋድ የንጉሡን እርምጃ አድንቀዋል።

የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጆሮ የነሱት ውሳኔ ከመቼ ጀምሮ እንደሚተገበር የተነገረ ነገር የለም።

ምንም እንኳ ሳኡዲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ክልከላዎችን ብታነሳም አሁንም ንጉሣዊው አስተዳደር ከወቀሳ አልዳነም።

በተለይ ደግሞ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ከሁለት ዓመት በፊት ቱርክ በሚገኘው የሳኡዲ ቆንስላ የተፈጸመበት አሰቃቂ ግድያና በርካታ የሰብዓዊ መብትና የሴቶች መብት ተሟጋቾች እሥር ቤት መሆን የሳኡዲን ስም ያጠለሹ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ለሰብዓዊ መብት በመሟገት የሚታወቅ አንድ የሳኡዲ ዜጋ እሥር ቤት ውስጥ እያለ መሞቱ ደግሞ ነገሮችን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጓቸዋል።