ቻድ ያለባትን የ100 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለአንጎላ ከብቶች በመስጠት ልትከፍል ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻድ ለአንጎላ መክፈል ያለባትን 100 ሚሊዮን ዶላር እዳ በገንዘብ መመለስ ባለመቻሏ ከብቶች በመስጠት እየከፈለች መሆኗን የአንጎላ መንግሥት ጋዜጣ ዘገበ።
ቻድ የገንዘብ እጥረት ስለገጠማት እንዲሁም አንጎላ ደግሞ ከብቶችን ስለምትፈልግ፤ ባልተለመደ ሁኔታ የእዳው ክፍያ ለሁለቱም አገራት አመቺ በሆነ ሁኔታ እንዲፈጸም መደረጉ ተነግሯል።
ጋዜጣው እንደዘገበው ከአንድ ሺህ የሚበልጡ በሬዎች በመጀመሪያ ዙር የዕዳ ክፍያነት በመርከብ ተጭነው ወደ አንጎላዋ መዲና ሉዋንዳ ገብተዋል።
ቻድ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት እያንዳንዳቸው 1,333 ዶላር የሚያወጡ በአጠቃላይ 75 ሺህ ከብቶችን ለአንጎላ ትሰጣለች ተብሏል።
ዘገባው ጨምሮ እናዳለው ቻድ በዚህ ወር ማብቂያ ላይ ተጨማሪ 3,500 ከብቶችን ወደ አንጎላ ትልካለች ብሏል።
ቻድ ያለባትን ዕዳ በገንዘብ መመለስ ባለመቻሏ በከብቶች ለመክፈል ስትወስን፤ አንጎላ ጥያቄውን የተቀበለችው በድርቅ በተጠቁ ግዛቶቿ ውስጥ ያለውን የከብቶች ቁጥር ለማሳደግ እንደሚያግዛት በማሰብ ነው።
አንጎላ እንስሳቶቿን በረሃብና በጥማት በሚገድል ድርቅ በተደጋጋሚ እየተመታች በርካታ ዜጎቿ ለችግር የሚጋለጡባት አገር ናት።
ምንም እንኳን አገሪቱ በነዳጅ ሃብት የታደለች ብትሆንም፤ ነጻነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ለ27 ዓመታት ሲካሄድ ከቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ውድመት ለማገገም እየጣረች ትገኛለች።
ቻድ 94 ሚሊዮን የሚደርስ የቀንድ ከብት ያላት አገር ስትሆን፤ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት 30 በመቶውን የሚሸፍነው የቀንድ ከብቶች ሽያጭ ነው። ይህም ከነዳጅ ምርት ቀጥሎ ሁለተኝነት የውጪ ምንዛሪ ያስገኝላታል።
ባለፈው ጥቅምት ወር የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት ላይ በነዳጅ ዋጋ መቀነስና በአካባቢዋ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ እስላማዊ ቡድኖች በሚፈጠር የጸጥታ ችግር ሳቢያ ኢኮኖሚዋ በቀላሉ ሊጎዳ እንደሚችል አመልክቶ ነበር።














