እርዳታ ለመቀበል ሲሻሙ የነበሩ 20 ናይጄሪያውያን ተረጋግጠው ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በደቡብ ምሥራቅ ኒጀር እርዳታ ለመቀበል ሲጠባበቁ ከነበሩ ሰዎች 20 የሚሆኑት ተረጋግጠው መሞታቸው ተዘገበ።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ህጻናት እና ሴቶች ናቸው ተብሏል።
ሟቾቹ በናይጄሪያ አመጸኛው ቦኩ ሐራም የሚያደርሰውን ጥቃት ሸሽተው በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ በዜግነት ናይጄሪያውያን እንደነበሩ ተነግሯል።
የእርዳታ ምግብ እና ገንዘብ ለመቀበል ሲጠባበቁ የነበሩ ስደተኞች የእርዳታ ሰጪው ድርጅት በራፍ ሲከፈት ወደፊት ቀድሞ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ነው 20 የሚሆኑት ሰዎች ተረጋግጠው የሞቱት።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከሆነ የምግብ እና የገንዘብ እርዳታውን ያደርግ የነበረው መጠለያ ጣቢያውን ሲጎበኝ የነበረው የናይጄሪያ ቦርኖ ግዛት አስተዳዳሪ ነበር።
ዲፋ በምትሰኘው ከተማ በተከሰተው አደጋ ከሟቾች በተጨማሪ በ10 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል።
ቦኩ ሐራም የሚያደርሰውን ጥቃት ሽሽት ተከትሎ አደጋው በተከሰተባት የኒጀር ግዛት ብቻ ከ120ሺህ በላይ ናይጄሪያውን ስደተኞች ተጠልለው ይገኛሉ።
እአአ 2009 ጀምሮ ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሐራም በናይጄሪያ በርካታ ጥቃቶችን ሲያደርስ ቆይቷል።













