የኮሮናቫይረስ በሽታን ምልክት ያሳዩ 14 ኢትዮጵያውያን ነፃ ሆነው ተገኙ

የኮሮናቫይረስ በሽታን ምልክት አሳይተው የነበሩ አስራ አራት ኢትዮጵያውያን ከላብራቶሪ ምርመራ በኋላ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢንስቲትዩቱ ይህንን ያሳወቀው በዛሬው ዕለት የኮሮናቫይረስን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን አስራ አራቱ ግለሰቦች ወደ ለይቶ ማቆያ ስፍራም ተወስደው ነበርም ብሏል።
በትናንትናውም ዕለት አንድ የተጠረጠረ ሰው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን በኢንስቲትዩቱ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱም ከቫይረሱ ነፃ መሆኑን በመረጋገጡ ከለይቶ ማቆያ ማዕከሉ እንዲወጣ መደረጉንም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ገልፀዋል።
በበሽታው መስፋፋት ምክንያት በተፈጠረ ስጋት በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች ያቋረጡ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ "በረራ ማቋረጥ በሞራልም በሥነ ምግባርም ተቀባይነት የለውም" በሚል የቀጠለ ሲሆን ለተጓዦችም አስፈላጊውን ምርመራና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አየር መንገዱም ሆነ ኢንስቲትዩቱ አረጋግጠዋል።
የቦሌ አየር ማረፊያን ጨምሮ በሁሉም አቅጣጫ ባሉ የሀገሪቱ መውጫና መግቢያ ድንበሮች የሙቀት ልየታ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሰው ኢንስቲትዩቱ፤ ከጥር 14/2012- የካቲት 2/2012 ድረስ የኮሮናና የኢቦላ ቫይረስን ዝግጁነት በጋራ በማጣመር ከአንድ መቶ ሰባ ሁለት ሺህ በላይ መንገደኞች ምርመራ ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን ከሙቀት ልየታ በተጨማሪ የበሽታው ምልክት የታየባቸው መንገደኞችን የጤና ሁኔታ የመከታተል ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ መቀጠሉን ዶክተር ኤባ አሳውቀዋል።
ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በአገር ውሰጥ በሚቆዩበት ወቅት አድራሻቸው ተመዝግቦ ለአስራ አራት ቀናት ክትትል የሚደረግባቸውን መንገድ እንደተዘረጋም ዶ/ር ኤባ በተጨማሪ ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ከታየባቸው አገራት የመጡ መንገደኞች ወይም ንክኪ ያላቸው ሰዎች የሚያሳዩዋቸውን ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የመተንፈስ ችግር ህብረተሰቡ ሲያይ በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ የነፃ መስመሮች በዘረጋው መሰረትም ጥቆማዎች መጥተውለታል።
እስካሁንም ባለው 39 ጥቆማዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል መጥተው አስፈላጊውን ማጣራት አድርጌያለሁ ብሏል።
እነዚህንም ክትትሎች ለማሳለጥ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች፣ ለሆቴል ባለሙያዎችና ከክልልና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተውጣጡ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አሳውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለባቸው በሁሉም ክልሎች ውስጥ የለይቶ ማቆያ ማዕከልና የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከላትን ለመዘርጋት ኢንስቲትዩቱ በያዘው ዕቅድ መሰረት ወደ ሃዋሳ ከተማ የባለሙያዎች ቡድን የላከ ሲሆን ዝግቶችም እየተደረጉ ነው ብሏል።
ከሁቤይ ግዛት፣ ውሃን ከተማ የተነሳው ኮሮናቫይረስ ለ1018 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ እንዲሁም 43ሺ 108 ሰዎች በቫይረሱ መያዝ እንዲሁም 4053 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።












