መንግሥት ለቀድሞ የኬንያ መሪ ቀብር ቀድመው ለሚገኙ ነጻ ምግብና እና መጠጥ አዘጋጃለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለቀድሞ የኬንያ ፕሬዝደንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ቀብር ቀድመው ለሚደርሱ ምግብና እና መጠጥ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
ሞይ ነገ ሲቀበሩ ለቀብሩ ቀድመው ለሚደርሱ 30ሺህ ለቀስተኞች ዳቦ እና ለስላሳ መጠጥ በመንግሥት ወጪ እንደሚቀርብ አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት አራፕ ሞይ የምሥራቅ አፍሪካዋን አገር ኬንያን ለ24 ዓመታት የመሩ ሲሆን፤ አገሪቱ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ስልጣን የያዙ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ከቀብር ስነስርዓት አስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት ጆርጅ ናቴምቤያ እንዳሉት በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ለሚገኙ 30 ሺህ ሰዎች የመቀመጫ ወንበር መዘጋጀቱን ጨምረው ተናግረዋል።
ቀብሩ የሚከናወነው በፕሬዝደንቱ የትውልድ መንደር በሆነችው ካባራክ ሲሆን፤ ከመንደሯ 20 ኪ.ሜትር ርቃ ከምትገኘው ናኩሩ የትራንስፖርት አገልግሎት በነጻ እንደሚሰጥም ተነግሯል።
በርካታ ኬንያውያን ግን መንግሥት ነጻ መግብ እና ትራንስፖርት አቀርባለሁ ማለቱን እየተቹ ይገኛሉ።
ትችቱ መንግሥት ነጻ ምግብ እና ትራንስፖርት አገልግሎት አቀርባለሁ ያለው ለቀብር ስነ-ስርዓቱ የሚገኘው የህዝብ ቁጥር አነስተኛ እንዳይሆን በመስጋት ሰዎችን ለመደለል ነው የሚል ነው።
ሞይ ኬንያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በብቸኝነት ሲመሩ ቆይተው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ነበር እንደ ጎርጎሳውያኑ 1992 ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ምርጫው መድረክ እንዲመጡ የፈቀዱት።
በስልጣን ዘመናቸው ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግርፋት እንዲሁም ሰቆቃን በመፈጸም ቢወቀሱም በርካታ የሃገሬውን ሰው ደግሞ በፍቅር ማሸነፍ ችለዋል ይባልላቸዋል።












