ካናዳ፣ አሜሪካ እና ዩኬ አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ እምነት አለን አሉ

ዩክሬን አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምዕራባውያን መሪዎች የዩክሬኑ አውሮፕላን ቴህራን አቅራቢያ የመከስከሱ ምክንያት ኢራን በስህተት በሚሳኤል መትታ ስለጣለችው ነው አሉ።

የአሜሪካ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም መሪዎች አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ ማስረጃ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከምዕራባውያን ሃገራት በተጨማሪ የኢራቅ እና የዩክሬን መንግሥታትም አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ እምነት አድሮባቸዋል።

ለ176 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የአውሮፕላን መከስከስ ዙሪያ ዝርዝር ምርመራዎች እንዲደረጉ የዩናይድ ኪንግደም እና ካናዳ መንግሥታት ጠይቀዋል።

ትናንት አመሻሽ ላይ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ኃላፊ ለሲቢኤስ የዜና ወኪል ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን በኢራን ሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ ጥቆማ ከሰጡ በኋላ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ዩክሬን ቀደም ብላ አውሮፕላኑን እንዲከሰከስ ያደረገው ከኢራን የተተኮሰ ሚሳኤል ሊሆን እንደሚችል ግምት አስቀምጣ የነበረ ሲሆን፤ ኢራን ግን የዩክሬንን ምልከታ አጣጥላው ነበር።

ኢራን ሩሲያ ሰራሽ ቶር የመከላከያ ሚሳኤል ሥርዓት ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ሩሲያ ሰራሽ ቶር የመከላከያ ሚሳኤል ሥርዓት ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ኢራን አውሮፕላኑን መትታ የጣለችው የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ጋር አሳስታ ስለመሆኑ በስፋት እየዘገቡ ነው።

አንድ አውሮፕላን በሚሳኤል ተመትቶ ከወደቀ ለጥቃቱ ጥቅም ላይ የዋለው ሚሳኤል በራዳር፣ ኢንፍራሬድ ወይም ሳተላይት ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ሲግናሉን ማግኘት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሲቢኤስ የዜና ወኪል አንድ የአሜሪካ የደህንነት ባለሙያን ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለት ሚሳኤሎች ሲወነጨፉ እና ሚሳኤሎች ያስከተሉት ፍንዳታ በሳተላይት ተመዝግቦ ተገኘቷል።

በሌላ በኩል ኒውስዊክ የተሰኘው ሌላው የአሜሪካ የዜና ተቋም የፔንታጎን፣ የአሜሪካ እና የኢራቅ መንግሥታት የደህንነት ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፤ አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው በሩሲያ ሰራሽ ቶር ሚሳኤል ነው።

የአውሮፕላኑ ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ አውሮፕላን ቴህራን ከሚገኘው ኢማም ኮሜይኒ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው የተከሰከሰው።

አውሮፕላኑ ጉዞውን ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አድርጎ ነበር የተነሳው።

ኢራን የአውሮፕላኑን የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ለአሜሪካም ሆነ ለቦይንግ አልሰጥም ማለቷ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ኢራን የዩክሬን እና ቦይንግ መርማሪዎች በምርመራው ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢራን እንዲገቡ ፍቃድ ሰጥታለች።

እንደ ዓለም አቀፍ አቪዬሽን ሕግ ከሆነ ኢራን ምርመራውን የመምራት መብት ያላት ሲሆን፤ በተለምዶ ግን የአውሮፕላኑ አምራቾች በምርመራው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖራቸዋል።

ምዕራባውያን መሪዎች ምን አሉ?

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ አውሮፕላኑ ከምድር ወደ ሰማይ ተወንጫፊ በሆነ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመጣሉ ብዙ የደህንነት መረጃዎች ደርሰውኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ፤ ባገኙት መረጃ መሠረት ኢራን አውሮፕላኑን ሆነ ብላ አልመታችም።

"ካናዳውያን ጥያቄዎች አሏቸው። ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ ማግኘት ይገባቸዋል" በማለት በአደጋው ዙሪያ ዝርዝር ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ለአደጋው የትኛውንም አካል ተጠያቂ ለማድረግም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 178 ሰዎች መካከል 63 ካናዳውያን ሲሆን፤ ከዩክሬኗ ኪዬቨ ወደ ቶሮንቶ ካናዳ የሚያቀኑ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ትናንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ''ከዚህ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ጥርጣሬ አለኝ። የሆነ አካል ስህተት ሳይሰራ አይቀርም'' ከማለት ውጪ ዝርዝር ነገር መናገርን አልፈቀዱም።

የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንም፤ ሃገራቸው ከካናዳ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የዩክሬን የደህንነት ኃላፊ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ሦስት ምክንያቶችን አስቀምጠው ነበር። እነዚህም፦

  • አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ እንደ ድሮን ካሉ ሌላ በራሪ አካል ጋር ተጋጭቷል።
  • የሞተር ብልሽት ወይም በቴክኒክ ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ ጋይቷ ወይም ደግሞ
  • በሽብር ጥቃት ከአውሮፕላኑ ውስጥ ፍንዳታ አጋጥሟል የሚሉ መላ ምቶችን አስቀምጠው ነበር።
Presentational white space

ኢራን ምን እያለች ነው?

የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አቤደዛዱህ "አውሮፕላኑ በምዕራብ አቅጣጫ ከአየር ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ቀኝ ዞሮ ተመልሶ ለማረፍ እየመጣ ሳለ ነው የተከሰከሰው" ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም የዓይን እማኞች አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ በእሳት ተያይዞ ማየታቸውን ገልጸዋል።

"በሳይንሳዊ መንገድ ከተመለከትነው፤ ይህ አውሮፕላን በሚሳኤል ተመትቶ ነው የወደቀው የሚለው የሚያስኬድ አይደለም" ብለዋል።

Presentational grey line

የአሜሪካ እና ኢራን ፍጥጫ

ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው ይህ ሁሉ እሰጣ ገባ የጀመረው አሜሪካ በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒን ከገደለች በኋላ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ፤ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒን 'አሸባሪ' ይበሉት እንጂ በኢራናውያን ዘንድ እንደ 'ጀግና' ነበር የሚቆጠረው።

የጦር ጀነራሉ፤ ከፕሬዝደንቱ በላይ እና ከኃይማኖት መሪው በታች የሚገኙ ሁለተኛው የኢራን ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ነበሩ።

ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኩድስ ኃይል አዛዥ ነበሩ።

ኢራን ለጀነራሉ ግድያ በአሜሪካ ላይ የአጸፋ ምላሽ ለመውሰድ ብዙ ከዛተች በኋላ፤ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መንደሮች ላይ የሚሳኤል ድብደባ አድርጋ ነበር።