ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለስድስት ሰአታት ልቧ መምታት ያቆመው ሴት በህይወት ተረፈች
አንዲት እንግሊዛዊት ልቧ ለስድስት ሰአታት መምታት ካቆመ በኋላ እንደገና መተንፈስ መጀመሯ የህክምና ባለሙያዎችን ግራ አጋብቷል።
የህክምና ባለሙያዎችም አጋጣሚውን እጅግ የተለየና ከስንት ጊዜ አንዴ ሊከሰት የሚችል ነው ብለውታል።
ኦድሪ ሹማን ባለፈው ወር ነበር ስፔን ውስጥ ተራራ በመውጣት ላይ ሳለች ከበረዶ ጋር የተቀላቀለ ንፋስ የመታት። ከአደጋው በኋላ ሰውነቷ መቋቋም ከሚችለው በላይ ቅዝቃዜ ስላጋጠመው ልቧ መምታቱን አቁሟል።
የ 34 ዓመቷ ኦድሪ ስፔን ባርሴሎና ውስጥ የምትኖር ሲሆን አደጋው ካጋጠማት በኋላ መተንፈስ አቅቷት ነበር። በወቅቱ አብሯት የነበረው ባለቤቷ ሁኔታዋ አሳሳቢ ስለነበር ወዲያው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን እንደጠራ ገልጿል።
'' የልብ ምቷን ለማዳመጥ ስሞክር ምንም ነገር የለም። ምንም አይነት ትንፋሽም አልነበራትም። በወቅቱ እንደሞተች እርግጠኛ ነበርኩ'' ብሏል።
ከስድስት ሰአታት ለሞት የቀረበ ቆይታ በኋላ ኦድሪ አገግማ ወደ ሙሉ ጤንነቷ ስትመለስ በድጋሚ ተራራ መውጣት መጀመር እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
የባለቤቷን የድረሱልን ጥሪ ተከትሎ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከሁለት ሰአት በኋላ በቦታው ሲደርሱ የኦድሪ ሰውነት የሙቀት መጠን 18 ዲግሪ ሴልሺየስ ደርሶ ነበር።
ባርሴሎና የሚገኘው ቫል ዴብሮን ሆስፒታል ስትደርስም ምንም አይነት ትንፋሽም ሆነ የልብ ምት አልነበራትም።
ነገር ግን በሞት አፋፍ ላይ አድርሷት የነበረው ከባድ ቅዝቃዜ ሕይወቷን ለማትረፍ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ሲከታተሏት የነበሩት ዶክተር ኤድዋርድ አርጉዶ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
'' ምንም እንኳን ሁኔታዋ ሙሉ በሙሉ እንደሞተ ሰው ቢሆንም ከባድ ቅዝቃዜ ከሞት የመከላከልም አቅም እንዳለው እናውቃለን።''
''ምንም እንኳን ኦድሪ በበረዶው ምክንያት ሞት አፋፍ ላይ ብትደርስም እራሷን ስታ በነበረበት ወቅት ከባዱ ቅዝቃዜ ሰውነቷ እና አንጎሏ ከጥቅም ውጪ እንዳይሆኑ አቀዝቅዞ አቆይቷቸዋል'' ብለዋል ዶክተር ኤድዋርድ።
''ሰውነቷ የተለመደውና ጤናማ ሰው ያለው ሙቀት ኖሮት ልቧ መምታቱን ቢያቆም ኖሮ ያለምንም ጥርጥር ትሞት ነበር'' ሲሉ አክለዋል።
ኦድሪ ከ 12 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ወደ ቤቷ የተመለሰች ሲሆን እጇ ላይ ካጋጠማት መለስተኛ ጉዳትና የመንቀሳቀስ ችግር ውጪ ጤናማ ሆናለች።
ከሆስፒታል ስትወጣም ከአደጋው በኋላ ስለነበሩት ስድስት ሰአታትም ሆነ ቀጣይ ቀናት ምንም የምታስታውሰው ነገር እንደሌለ ገልጻለች።
'' ለሁለት ቀናት ያክል ምን እንደተፈጠረ የማውቀው ነገር አልነበረም። ስነቃ ሆስፒታል ውስጥ ነኝ። አሁን አንዳንድ መጽፍት ማንበብ ጀምሬያለሁ፤ በተለይ ደግሞ ስለ ቅዝቃዜና ስላሉት ጥቅምና ጉዳቶች'' ብላለች።
በቅርቡም ወደ ተራራ መውጣት መመለስ እንደምትፈልግ ገልጻለች።