በሽታን ለመካላከል የሚያስችሉ የአንጎል ህዋሳትን መስራት ተቻለ

በጣም ትንሽዬና አንጎል ውስጥ የምትቀመጠው "ችፕስ"

የፎቶው ባለመብት, UNIVERSITY OF BATH

ተመራማሪዎች የሰውን ልጅ አካላት ለመጠገን ያስችላል ለተባለ አዲስ ዘዴ መንገድ የሚጠርግ ነው የተባለ የሰው ሰራሽ የህብለ ሰረሰር ህዋሳትን መስራታቸው ተነገረ።

በጣም ትንሽዬና አንጎል ውስጥ የምትቀመጠው "ችፕስ" እንደ ህያው ነገር በሰውነት ውስጥ አስፈላጊውን የህዋስ ተግባራትን በማከናወን ወደፊት ደግሞ አልዘሚርን የመሳሰሉ የአንጎል በሽታዎችን ለማከም ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።

በፈጠራው ላይ የተሳተፉት ብሪታኒያ ውስጥ በሚገኘው ባዝ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሒሳብ፣ በኮምፒውተር ሳይንስ እንዲሁም ጥቃቅኖችን ቺፖች ዲዛይን በማድረግ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ናቸው።

እነዚህ የባለሙያዎችን የያዘው ቡድን በመጨረሻ ላይ በሰው ልጅ አንጎል ውስጥ ያሉ ኑዩሮኖች (የአንጎል ሴሎች) የሚያከናውኑትን ተፈጥሯዊ ሥራ የሚሰሩ ሰው ሰራሽ ህዋሳትን ለመፍጠር ችለዋል።

ኒዩሮኖች ከአንጎላችንና ከሌላው አካላችን የሚተላለፉ መልዕክቶችን የሚያመላልሱ ህዋሳት ናቸው።

ሳይንቲስቶች በኒዩሮኖች ማርጀት ወይም መሞት ሳቢያ የሚከሰቱትን አልዘሚርን የመሳሰሉ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችል እድልን ሊፈጥር ይችላል በሚል እነዚህን ህዋሳት ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።

በባዝ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት አሌን ኖጋሬት እንዳሉት "እስካሁን ድረስ ኒዩሮኖች ውስጣቸው እንደማይታወቅ ጥቋቁር ሳጥኖች ነበር የሚታዩት፤ የእኛ ጥናት ግን ይህንን ምስጢር በመግለጥ የህዋሳቱን ኤሌክትሪካዊ ባህሪያት እያንዳንዱን ጥቃቅን ይዘት በዝርዝር ለማወቅ የሚያስችል ዘዴን አቅርቧል" ብለዋል።

በህክምና የጥናት ዘርፍ ከተፈጥሯዊው የነርቭ ሥርዓት ለሚወጡ መልዕክቶች ምላሽ የሚሰጡ ሰው ሰራሽ ኒዩሮኖችን መፍጠር ለረዥም ጊዜ ጥረት ሲደረግበት የነበረ ወሳኝ ግብ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሲገጥሙ የነበሩት ፈተናዎች መልዕክት የሚተላለፍበትን መስመር መቅረጽና በሚፈጠረው ግንኙነት የሚተላለፈው መልዕክት በትክክል ተፈጥሯዊ መንገድን የተከትሎ በምን ያህል መጠን ተግባራዊ እንደሚሆን መረዳት ነበር።

"እኛም በምርምራችን ለእነዚህ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጡ ግኝቶችን ከማግኘታችን ባሻገር በሰው ሰራሽ መንገድ ኒዩሮኖቹን ለመስራት ያስችለናል" ብለዋል ፕሮፌሰር ኖጋሬት።

ተመራማሪዎቹ በአንጎላችን ውስጥ የማስታወስ ሥራን የሚያከናውነውን ሂፖካምፐስ በተባለው ክፍልና አተነፋፈሳችንን በመቆጣጠር በኩል ላይ ሚና አላቸው ሁለት አይነት ህዋሳትን አስመስሎ ለመስራት ተችሏል።

ይህ የጥናት ውጤት እየተባባሱ የሚሄዱ የልብ ሥራ ማቆምንና የአልዘሚር በሽታን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ ኒዩሮኖችን የመጠገን ዕድልን ይሰጣሉ።