በፌስቡክና በዩቲዩብ ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያገኙ ያውቃሉ?

የፌስቡክና የዩቲዩብ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚያገኙት ገቢ በአስደናቂ መጠን መጨመሩን አዲስ የወጣ አንድ ሪፖርት አመለከተ።

የግብይት ተቋም የሆነው ኢዚያ ደረስኩበት እንዳለው፤ በኢንስታግራም ላይ ከአምስት ዓመት በፊት ስፖንሰር ተደርጎ ይወጣ የነበረ አንድ ፎቶግራፍ 134 ዶላር ዋጋ የነበረው ሲሆን አሁን ግን ወደ 1642 ዶላር አሻቅቧል።

ባለንበት ዘመን ታዋቂ የንግድ ምልክቶች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ስፖንሰር አድርገው ለሚያወጧቸው መልዕክቶች፣ ታሪኮች እና ጦማሮች ጭምር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው ተብሏል።

ይህ ክስተት ለማስታወቂያ ድርጅቶች ስጋት ሊፈጥር ይችላል ቢባልም አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንዳሉት ግን የተለመደውና መደበኛው የማስታወቂያ መንገድ አብቅቶለታል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንዳለው በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በተለይም በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በኢንስታግራምና የጡመራ መድረኮች ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ገንዘብን በዝርዝር ተመልክቷል።

ከአንድ መቶ ሺህ በታች ተከታዮች ካሏቸው ሰዎች አንስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ተከታዮችን በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ማፍራት እስከቻሉ ታዋቂ ሰዎች ድረስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እያገኙ እንደሆነ ተገልጿል።

በሪፖርቱ ላይ ከተጠቀሱት የጥናት ውጤቶች መካከልም፦

 በኢንስታግራም ላይ በስፖንሰር የሚወጡ ፎቶዎች የሚያስገኙት ገንዘብ በ44 በመቶ ጨምሯል።

 በስፖንሰር የሚወጣ የጡመራ መድረክ ጽሑፍ ከ8 ዶላር ወደ 1442 ዶላር አሻቅቧል።

 የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ከፍተኛ ገቢን በማስገኘት ቀዳሚ ሆነዋል፤ በዚህም ከጥቂት ዓመት በፊት 420 ዶላር ያስገኝ የነበረው ዛሬ 6700 ዶላር ደርሷል።

 በፌስቡክ ላይ የሚወጣ አንድ አጭር መልዕክት ያስገኝ የነበረው 8 ዶላር ገቢ አሁን ወደ 395 ዶላር ከፍ ብሏል።

 በትዊተር ላይ የሚሰፍር አንድ መልዕክት ከ29 ዶላር ወደ 422 ዶላር ገቢን ያስገኛል።

 የጡመራ መድረክ ላይ የሚሰፍር ጽሑፍ ደግሞ ከ407 ዶላር ወደ 1442 ዶላር ያስገኛል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ በመሆኑ ዘርፉ ከተቆጣጣሪ አካላት በኩል ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት አስገድዷል።

አንዳንድ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ የወጡ መልዕክቶችም ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው ተብለው ባለፈው ሳምንት ከኢንስታግራም ላይ ባለፈው ወር ታግደዋል። በተለይ የምርት ማስታወቂያዎችን የሚመለከቱ መልዕክቶችን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች ስጋትን እየፈጠሩ ነው።

ይህ ሁሉ ቢሆንም ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁ ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በማኅበራዊ መድረኮች ላይ ለሚያወጧቸው ማስታወቂያዎች እያፈሰሱ ነው።

የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው በተጽዕኖ ፈጣሪዎች በኩል የሚወጡ መልዕክቶች በ150 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል። በዚህም ወደ ዘርፉ የሚገባው የገንዘብ መጠን ስለሚጨምር በቀጣይ ዓመት ዘርፉ ባለ 10 ቢሊየን ዶላር ኢንደስትሪ ይሆናል።