ነጻ ፍልሚያ ሊመለከቱ ስታድየም የገቡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ 'ዩኤፍሲ' የተሰኘውን ነጻ የፍልሚያ ውድድር ሊመለከቱ የሄዱበት ስታድየም በተቃውሞ ተቀብሏቸዋል።
ኒው ዮርክ ግዛት ወስጥ በሚገኘው ማዲሰን ስኩዌር ጋርደን አዳራሽ ከሁለት ወንድ ልጆቻቸውና ከሹማምንት ጋር የተገኙት ትራምፕ 'ቡ. . . ' እያሉ በሚጮሁ ተመልካቾች ምሽታቸውን ለመጀመር ተገደዋል።
ከአዳራሹ ውጪም ቢሆን የተወሰኑ ግለሰቦች ሰላማዊ ሰልፍ አሰናድተው ፕሬዝደንቱን ሲቃውሙ አምሽተዋል።
ትራምፕ መሰል የተቃውሞ ድምፅ ሲገጥማቸው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት የመንግሥታቸው መቀመጫ በሆነችው ዋሽንግተን የቤዝቦል ጨዋታ ለመመልከት ገብተው ለተመልካቾች እጃቸውን ቢያውለበልቡም ታድሚያኑ ግን በተቃውሞ ድምፅ ተቀብለዋቸው ነበር።
አልፎም በዋሽንግተኑ ክስተት ላይ 'ከርቸሌ ይወርዱ' የሚል ስንኝ ያለው ዜማ ሲቀነቀን ነበር። ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ሂላሪ ክሊንተን 'ከርቸሌ ይውረዱ' የሚሉ ዜማዎች ይደመጡ እንደነበር አይዘነጋም።
ቅዳሜ ዕለት በነበረው ቡጢ ላይ ምንም እንኳ አብዛኛው ተመልካች በተቃውሞ ቢጮህባቸውም በጭብጨባ እና በፉጨት ክብር የሰጧቸውም አልጠፉም ተብሏል።
'ትራምፕ ይወገዱ'፣ 'ከሥልጣን ፈንግሉልን' የሚል ፅሁፍ የሚነብባቸው ሰሌዳዎች ከፍ ብለው ታይተዋል።
ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር በመመሳጠር የመጭው ምርጫ ተቃናቃኛቸው ጆ ባይደን ላይ ሤራ ጠንስሰዋል ተብለው እየተወቀሱ ያሉት ትራምፕ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከሥልጣናቸው ሊባረሩ ይችላሉ።













