ዛሬ በመቀሌ ሊካሄድ የነበረ ሠላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ተበተነ

የፎቶው ባለመብት, HAPHTOM BERHE
'ህድሪ ሰብ' በተባለ ማህበር ዛሬ ቅዳሜ መቀሌ ከተማ ውስጥ ሊካሄድ ተጠርቶ የነበረው ሠላማዊ ሰልፍ ህጋዊ አይደለም ተብሎ በፖሊስ ተበተነ።
ይህ ሠላማዊ ሰልፍ የተጠራው የትግራይ ክልል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተማሪዎች ችግር ያጋጥማቸዋል ወደተባሉ ቦታዎች እንዲሄዱ እንዳይደረግ በክልሉ መንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግ እንደነበረ ተነግሯል።
ሠላማዊ ሰልፉን የጠራው ማህበር ሊቀ መንበር መሃሪ ዮሐንስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስለሰልፉ ለማሳወቅ ለመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጸሐፊ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና ግልባጩንም ለዞኑ ፖሊስ ለማስገባት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት አንቀበልም መባላቸውን ተናግረዋል።
ሊቀ መንበሩ በተጨማሪ ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ መንግሥት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ማሳወቅ እንጂ የመፍቀድና የመከልከል ህጋዊ መብት የለውም ብለዋል።
ዛሬ ጠዋት ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ሮማናት ተብሎ በሚጠራው የመቀሌ ከተማ አደባባይ መሰባሰብ በጀመሩበት ጊዜ ፖሊሶች ወደ ስፍራው መጥተው ሰልፉ ህጋዊ ስላልሆነ በመግለጽ እንዲያስቆሙ መታዘዛቸውን በመግለጽ ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ ማድረጋቸውን የሰልፉ አስተባባሪዎች ተናግረዋል።
አስተባባሪዎቹም ከፖሊስ ጋር ግብግብ መፍጠር ተገቢ ባለመሆኑ ሰልፉን ለማካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ለፖሊስ የማሳወቂያ ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።
የመቀሌ ከተማ ምክትል ከንቲባ ስለተከለከለው ሠላማዊ ሰልፍ ተጠይቀው "ሰልፉ ሊከለከል አይገባም። ቢሆንም የጸጥታውን ሥራ በተመለከተ ማን ተጠይቆ ምን መልስ ተሰጠ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይገባል" ብለዋል።
የሠላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ተቀብሎ ወደሚመለከተው አካል ያላቀረበ ግለሰብ ካለ እንቀጣለን" ያሉት አቶ አቶ ብርሐነ፤ ለፖሊስ ቀርቦ ነበር የሚለው ቅሬታን ተከትሎ ፖሊስ የመከልከል መብት ስለሌለው ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተጠይቆ ሲከለከል በዚህ ሳምንት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን ለማውገዝ በተመሳሳይ መቀሌ ውስጥ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ቀርቦ እንደተከለከለ መዘገባችን ይታወሳል።













