ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት ሜትር ከሃያ አምስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ሴኔጋላዊ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች
ሴኔጋላዊው ታኮ ፎል ወደ ቅርጫት ኳሱ ዓለም የተቀላቀለው ገና ከሰባት ዓመታት በፊት ቢሆንም የ2.25 ሜትር ርዝማኔ ያለው ይህ ተጫዋች በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ (ኤንቢኤ) ከፍተኛ ስፍራ እያገኘ ነው።
ከዓለም ረዥሙ የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ሮማኒያዊው ጆርጅ ሙሬሳን በ6.3 ሴንቲ ሜትር የሚያጥረው የ23 አመቱ ታኮ፤ የታዋቂው የቦስተን ሴልቲክስ ከቋሚዎቹ አስራ አምስት ተጫዋቾች አንዱ ለመሆንም ጥረት ላይ ነው።
ሴልቲክስ ታኮ ፎልን የመረጠበት ምክንያትም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ እንደሆነም ተገልጿል።
በሴኔጋሏ መዲና ዳካር የተወለደው ታኮ፤ ወደ አሜሪካ የሄደው በ16 ዓመቱ ሲሆን፤ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሴንትራል ፍሎሪዳ ቅርጫት ኳስ ይጫወት ነበር።
ታኮ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ዩኒቨርስቲው ውስጥ ብዙዎች ሙያውን እንዲያሳድግ ድጋፍ አድርገውለታል።
ታዳጊ ሳለ ብዙም ስለ ቅርጫት ኳስ እንደማያውቅ ይናገራል። ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው ካርቱን ፊልሞች በማየት ነበር። የአያቱ ቅርጫት ኳስ መውደድ ስፖርቱ ላይ ፍቅር እንዲያሳድር አድርጎታል።
ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ቅርጫት ኳስ አድርጓል። ጉዞው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም።
"ቅርጫት ኳስ መጫወት አልችልም ነበር። ብዙ ነገር መማር ይጠበቅብኝ ነበር። እድለኛ ሆኜ ብዙ ሰዎች ራሴን እንዳሻሽል ረድተውኛል" ይላል።
ሂውስተን አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ወደ ቴኒሲ፣ ጂዎርጂያ እና ፍሎሪዳ አቅንቷል። በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሴንትራል ፍሎሪዳ ሁለት ዓመት ቆይቷል።
"አንድ ሴኔጋላዊ ታዳጊ ነበርኩ። ቅርጫት ኳስ መጫወት የጀመርኩትም ከስድስት ዓመት በፊት ነበር። ኤንቢኤ ውስጥ ለመጫወት ብዙ ለፍቻለሁ። በጣም እድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ቅርጫት ኳስ ሕይወቴ ነው። አንድ ቀን እንኳን ሳልጫወት ባልፍ አዝናለሁ" ሲል ይናገራል።