የአማራ ክልል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, ADP Facebook page
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ሚዲያ ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።
ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቤተሰባቸው ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ቢቢሲ ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፤ ከቤተሰባቸው ጋር እንደሚገናኙና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ለሳምንታት በክልሉ ሥራ አመራር ተቋም ውስጥ በስልጠናና በግምገማ ላይ እንደነበሩ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እስሩ የተከሰተው ከዚሁ ስልጠናና ግምገማ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል እኚሁ ግለሰብ ያላቸውን ግምት ጠቅሰዋል።
ረዳት ኮሚሽነሩን ለእስር የዳረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ አንድ የቤተሰብ አባል የተናገሩት ሲሆን፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንዳንድ ሰዎች ግን ጉዳዩ ባለፈው ዓመት ሰኔ 15 ባህርዳር ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገምታሉ።
ቢቢሲ ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ ከጥቂት ቀናት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በተመለከተ ከአንድ የቤተሰብ አባላቸው ለማረጋገጥ ቢችልም ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የጸጥታ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።












