1 ኪሎ ከ30 ሺህ ብር በላይ የሚሸጠው የዓለማችን ውዱ አይብ ከየትኛዋ እንስሳ የሚገኝ ይመስልዎታል?

ለአንድ ኪሎ ግራም የአህያ አይብ ከ30ሺህ ብር ይጠየቃሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለአንድ ኪሎ ግራም የአህያ አይብ ከ30ሺህ ብር ይጠየቃሉ

''የተለየ ጣዕም አለው፣ የትኛውም ምግብ ውስጥ ቀምሰውት የማያውቁት አይነት ጣዕም ነው ያለው"

ይህን ያሉት የቀድሞ የሰርቢያ የሕዝብ እንደራሴ ከአህያ ወተት ስለሚሰራው አይብ ሲናገሩ ነው።

ሰርቢያዊው የቀድሞ የሕዝብ እንደራሴ ስሎቦዳን ሲሚክ ባልተለመደው መስክ ከአህያ ወተት አይብ ማምረት ጀምረዋል።

የምርቱ አቅርቦት አነስተኛ ስለሆነ ለአንድ ኪሎ ግራም የአህያ አይብ 1000 ዩሮ ይጠየቅበታል።

"የአህያ አይብን የምንሸጠው በ50 ግራም አስተኛ መጠን ነው። ይህም ለ10 ሰው የሚበቃ ነው'' ብለዋል ሰርቢያዊው ስሎቦዳን ሲሚክ።

የአህያ አይብ ማሸጊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አይቡ በ50 ግራም ነው የሚሸጠው

ፍቅረኞቻቸውን ለማስደሰት የሚፈልጉ ወጣት ወንዶች በስጦታ መልክ ይህን አይብ እንደሚገዙ ስሎቦዳን ሲሚክ ይናገራሉ።

እውቁ ሰርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች በስሩ ለሚተዳደሩት ምግብ ቤቶች ይህን የአህያ አይብ በመግዛት ደንበኛ እንደሆነም ተነግሯል።

ስሎቦዳን ሲሚክ በዓመት ከአህያ ወተት የሚያመርቱት የአይብ መጠን 50 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፤ ወደ ሌሎች ሃገራት ለመላክ በወተት ውጤቶች ዙሪያ ያለው ጥብቅ ሕግ ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

''ይሁን እንጂ ቱጃሮች ሰርቢያ ድረስ እየመጡ ልዩ የሆነውን ምርቴን ይገዛሉ'' የሚሉት ስሎቦዳን ሲሚክ ከዚህ ቀደም ከማሌዢያ የመጣ አንድ ባለሃብት 15 ኪሎ ግራም የአህያ አይብ እንደገዟቸው ያስታውሳሉ።

ከአህያ ወተት የሚሰራው አይብ ለምን ተወደደ?

ሚስጢራዊ ቀመር።

በመላው ዓለም አህዮች ሰው እና ቁሳቁሶችን ከአንድ ወደ ሌላ ቦታ እንዲያንቀሳቅሱ ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት።

በአንዳንድ ቦታዎች የአህያ ወተት ጥቅም ላይ ይውላል። ከወተቱ አይብ ማውጣት ግን አስቸጋሪ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የአህያ ወተት ሴስቲን የተባለ ፕሮቲን በውስጡ ስለሌለ አይረጋም።

ስሎቦዳን ሲሚክ አህያ ሲያልቡ። ስሎቦዳን ከአህያ የሚሰራው አይብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው ይላሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስሎቦዳን ሲሚክ አህያ ሲያልቡ። ስሎቦዳን ከአህያ የሚሰራው አይብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው ይላሉ

ስለዚህም ስሎቦዳን ሲሚክ ይህን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለሙያ በመቅጠር መፍትሄ አበጁለት- ይህ ቀመር ትልቅ ሚስጥር ነው።

"ባለሙያው ብቻ ነው የሚያውቀው- እኔ ራሱ ምን እንደሆነ አላውቅም" ይላሉ ስሎቦዳን ሲሚክ።

አህዮች ከላሞች ያነሰ የወተት ምርት ነው የሚሰጡት። አንድ ኪሎ አይብ ለማምረት 25 ሊትር ወተት ያስፈልጋል ይላሉ።

ስሎቦዳን ሲሚክ በዚህ የተለየ መስክ የተሰማሩት ሃብት ለማካበት ሳይሆን ፍላጎቱ ስላደረብኝ ነው በማለት ያስረዳሉ።

የአህያ ወተት ሴስቲን የተባለ ፕሮቲን በውስጡ ስለሌለው አይረጋም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአህያ ወተት ሴስቲን የተባለ ፕሮቲን በውስጡ ስለሌለው አይረጋም

ኑሯቸውን ከሰርቢያ መዲና ቤልግሬድ 80 ኪሎ ሜትር ላይ የመሰረቱት የቀድሞ የሕዝብ እንደራሴ፤ ከአህያ በስተቀር ሁሉም አይነት ሊባል በሚችል የቤት እንስሳቶች ነበሯቸው።

"አህያ ለምን አይኖረኝም?'' ሲሉ ራሳቸውን ጠያቁ።

ከዚያም 20 አህዮችን ገዙ።

"በሰርቢያ አህያ ጅል የሆነ እንስሳ ተደርጎ ይታሰባል። ይህ ግን እጅጉን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። አህያ ምርጥ የሆነ እንስሳ ነው" በማለት ስሜታዊ ሆነው ይናገራሉ።

ከዚያም አህያ እያለቡ ወተቱን መሸጥ ጀመሩ።

ወተቱን በመሸጥ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ በመሆኑ፤ ከወተቱ አይብ የማምረቱ ሃሳብ ተግባራዊ አደረጉ።

"በየቀኑ የአህያ ወተት እጠጣለሁ። 65 ዓመቴ ነው። ምንም አይነት የጤና እክል የለብኝም"

ስሎቦዳን ሲሚክ በዘርፉ ላይ ውጤታማ መሆናቸውን ተከትሎ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ሌሎች 10 ሰዎች ዘርፉን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

"በሁሉም ዓለም የሚኖሩ ሰዎች የአህያን ወተት እንዲጠቀሙ እመክራለሁ" ብለዋል የቀድሞ የሕዝብ እንደራሴ።