"ፋና የሚፈልገን አይመስለንም" የምን ልታዘዝ ደራሲ

የምን ልታዘዝ ድራማ መግቢያ ጽሑፍ

የፎቶው ባለመብት, Dire Tube

"ምን ልታዘዝ" ተከታታይ ድራማ በፋና ቴሌቪዥን ላይ ዳግመኛ እንደማይታይ የድራማው ደራሲና ፕሮዲውሰር አቶ በኃይሉ ዋሴ ለቢቢሲ ቢያረጋግጡም፤ የፋና ቴሌቪዥን የመዝናኛ ክፍል ከፍተኛ አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ብርሃኑ በበኩላቸው "ድራማው የተቋረጠው ለምዕራፍ እረፍት ነው፤ በእርግጠኛነት ይቀጥላል" ብለዋል።

"ምን ልታዘዝ" ተከታታይ ድራማ፤ በፋና ቴሌቪዥን ላይ ከ2010 ዓ. ም. ጀምሮ በሦስት ምዕራፍ ለ38 ክፍል ሲተላለፍ የቆየ ድራማ ነበር።

ይህ ፖለቲካዊ ስላቅ የሚቀርብበት ተከታታይ ድራማ፤ ዘወትር እሁድ ከሰዓት ከሚተላለፍበት ፋና ቴሌቪዥን ለእረፍት ተብሎ እንደተቋረጠና ዳግመኛ በጣቢያው ለእይታ እንደማይበቃ የተሰማው በመገናኛ ብዙኀን ነበር።

የድራማው ፀሀፊ እና ፕሮዲውሰር አቶ በኃይሉ ዋሴ፤ ድራማውን በፋና ቴሌቪዥን ለማስተላለፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ለቢቢሲ አረጋግጧል።

አቶ በኃይሉ እንደሚለው፤ ከፋና ጋር መሥራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አልነበሩም። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ "ምን ልታዘዝ" በሚተላለፍበት ሰዓት ላይ ይዘቱ ከድራማው ጋር አንድ ዓይነት የሆነ ሌላ ድራማ እየተላለፈ መሆኑ "የሚነግረን ነገር አለ" በማለት፤ ጣቢያው እንደገፋቸው ያስረዳል።

የድራማው አዘጋጆች ለሦስት ወር እረፍት (ሲዝን ብሬክ) ጠይቀው ድራማው መተላለፍ ማቋረጡን የሚናገረው በኃይሉ፤ በዚህ መካከል ፋና ብሮድካስቲንግ ሌላ ድራማ በነሱ ሰዓት ላይ ማስተላለፍ መጀመሩን አለመንገሩ፤ "ፋና የሚፈልገን አይመስለንም" እንዳስባላቸው ይገልጻል።

የፋና ብሮድካስቲንግ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጁ አቶ ዘካሪያስ በበኩላቸው፤ የእሁዱ የአየር ሰዓት ላይ ሌላ ድራማ እየተላለፈ መሆኑን አረጋግጠው፤ ይህ ግን "ምን ልታዘዝ" ከእረፍት እስኪመለስ ድረስ እንደሆነ ይገልጻሉ።

አቶ ዘካሪያስ አክለውም፤ በእርግጥ እየተላለፈ ያለው ድራማ 'ሲትኮም' ቢሆንም በይዘት ግን ከ"ምን ልታዘዝ" ጋር አይገናኝም ብለዋል። በተጨማሪም የዚህ ድራማ ክፍሎች በቅድሚያ ማክሰኞ ምሽት ከታዩ በኋላ እሁድ እንደሚደገሙ ገልጸዋል።

"የ "ምን ልታዘዝ" የምዕራፍ እረፍቱ ረዝሟል። እኛ ቶሎ እንዲመለሱ ብንፈልግም፤ እነርሱ የሦስት ወር የእረፍትና የዝግጅት ጊዜ በጠየቁት መሰረት አሁን ያሉት እረፍት ላይ ነው። የምናውቀው መስከረም ላይ እንደሚጀምሩ ነው" ይላሉ አቶ ዘካሪያስ።

አክለውም የእሁዱ ሰዓት አሁንም ቢሆን የ"ምን ልታዘዝ" ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።

የድራማው ደራሲና ፕሮዲውሰር ከፋና ጋር የነበረን ግንኙነት አልጋ በአልጋ አልነበረም ሲሉ ላቀረቡት ቅሬታ አቶ ዘካሪያስ ሲመልሱም፤ "ከሁሉም ተባባሪ አዘጋጆች ጋር እንደምንነጋገረው ከእነርሱ ጋርም እንነጋገራለን። ሥራዎችን እንገመግማለን። እንጂ ከዚህ ውጪ የተፈጠረ ነገር የለም" ብለዋል።

የ "ምን ልታዘዝ" ስፖንስር የነበሩ ሁለት ድርጅቶች ምክንያቱን በማያውቁት ሁኔታ ድጋፋቸውን እንዳቋረጡ አቶ በሀይሉ ይገልጻል። አክሎም ሌሎች ድርጅቶች የእነርሱን ድራማ ስፖንሰር ለማድረግ ይፈራሉ ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።

አቶ ዘካሪያስ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። ስፖንሰር ማድረግ አቋረጡ የተባሉት ድርጅቶች "እውነት ነው አቋርጠዋል" ካሉ በኋላ፤ ነገር ግን ይህ የተለመደ አሠራር ነው ይላሉ። እንዲያውም በድርጅቱ አሠራር በፕሮግራሞች ላይ ማስታወቂያዎች ቢተላለፉ፤ ለፋና እንዲሁም ለፕሮግራሞቹ አዘጋጆች አትራፊ መሆኑን ያብራራሉ።

"ከዚህ አንፃር ካየነው፤ በፋና ቴሌቪዥን ካሉ ከ25 በላይ ተባባሪ አዘጋጆች እስካሁን ድረስ በገቢ ደረጃ አንደኛ "ምን ልታዘዝ" ነው" ብለዋል።

የስፖንሰር መኖር ወይም አለመኖር ፋናንም ሆነ "ምን ልታዘዝ"ን በገቢ አይጎዳውም የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ በርካታ ማስታወቂያዎች በድራማው ላይ እንደሚተላለፉ በመጥቀስ አቶ በኃይሉ ያቀረቡትን ምክንያት ያጣጥላሉ።

በዚህ ሀሳብ የማይስማማው አቶ በኃይሉ፤ "የምንጠቀመው ስፖንሰር ቢኖረን ነው" ሲል ያስረግጣል።

አቶ በኃይሉ ድራማውን በሌላ መንገድ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ገልጾም "በድረ ገፅ ልናስተላልፈው እንችላለን" ሲል ፍንጭ ሰጥቷል።

አቶ ዘካሪያስ ግን "ድራማው ተቋረጠ" መባሉን ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው የሰማነው ይላሉ።

"እስካሁን ቀርቦ ያነጋገረን አካል [ከድራማው አዘጋጆች ወይም ፕሮዲውሰሮች] የለም" ካሉ በኋላ፤ "የእረፍት ጊዜያቸው ስላለቀ ከድራማው አዘጋጆች ጋር ቁጭ ብለን እንነጋገራለን" ብለዋል።