ፍልስጤማዊው የሃርቫርድ ተማሪ ወደ አሜሪካ እንዲገባ ተፈቀደለት

Ismail Ajjawi

የፎቶው ባለመብት, AMIDEAST

ጓደኞቹ ፌስቡክ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ምክንያት ብዙ ባወዛጋቢ መልኩ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ተከልክሎ የነበረው ፍልስጤማዊው ተማሪ ሰኞ ዕለት ወደ አሜሪካ እንዲገባ ተፈቀደለት።

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመከታተል አሜሪካ ቦስተን አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ለረዥም ሰዓታት በአሜሪካ ድንበር ተቆጣጣሪዎች ምረመራ እንደተደረገበት እስማኤል አጃዊ ተናግሯል።

የ17 ዓመቱ ተማሪ እስማኤል ሰኞ ዕለት ወደ አሜሪካ እንዲገባ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ትምህርቱን መከታተል ጀምሯል።

ከወራት በፊት የአሜሪካ መንግሥት ወደ አሜሪካ ማቅናት የሚሹ ሰዎች ቪዛ ሲያመለክቱ የሚጠቀሙትን የግል የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻ እንደሚጠየቁ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የአሜሪካ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገረው ተማሪ እስማኤል አጃዊ ''ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ሊያስከለክሉ የሚችሉ ምክንያቶች ባለመኖራቸው ኤፍ1 ቪዛ ተሰጥቶታል'' ብሏል።

በቅድሚያ ተማሪው ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለበት የሕግ አግባብ የቱ እንደሆነ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠበው ባለስልጣኑ፤ ''በወቅቱ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ባለስልጣናት ባገኙነት መረጃ ነው'' ብሏል።

የተማሪው ወላጆች ''በስተመጨረሻም ቢሆን በተሰጠው ውሳኔ ደስተኛ ነን'' ሲሉ ተናግረዋል።

''ያለፉት 10 ቀናት በጣም አስጨናቂ ነበሩ። አሁን ግን ደስተኞች ነን። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለላኩልን የማጽናኛ መልዕክት ከልብ እናመሰግናለን" ብለዋል የተማሪው ወላጆች።

ሃምዛ ራዛ የተባለ የሃርቫርድ ተማሪ እስማኤል ሃርቫርድ ከደረሰ በኋላ ፎቶግራፍ አብረው ተነስተው በትዊተር ገጹ ላይ ለጥፏል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

እስማኤል እንደሚለው የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ቦስተን አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ላፕቶፕ እና የእጅ ስልኩን ከመረመሩ በኋላ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እንደከለከሉት ተናግሯል።

ከሳለፍነው ሰኔ ጀምሮ የአሜሪካ መንግሥት ቪዛ አመልካቾች የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጾች፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረውን የስልክ እና የኢሜይል አድራሻ መጠየቅ ጀምሯል።

ይህ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሕግ በየዓመቱ ከ14.7 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ሰዎች መረጃዎችን እንደሚሰበስብ ታውቋል።