የእንግሊዝ ወላጆች በትምህርት ቤት ስልክ እንዲታገድ ለምን ይፈልጋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእንግሊዝ የሚኖሩ ግማሽ ያህሉ ወላጆች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሞባይል ስልክ እንዲታገድ ይፈልጋሉ ሲል 'ፕራይስ ኮምፓሪዝን ሳይት ዩስዊች' የተባለ ተቋም የዳሰሳ ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ እንደሚያስረዳው ልጃቸው የሚማርበት ትምህርት ቤት ስልክ እንዳይጠቀሙ እንደሚከለክል የተናገሩት ከስምንቱ ወላጆች አንዳቸው ብቻ ነበሩ።
በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች፤ አንድ ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት ይዞት የሚሄደው ዘመናዊ ስልክ በአማካይ 301 ፓውንድ የሚያወጣ መሆን እንደሚገባው አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
ባለፈው ዓመት 'ዜን ካልቸር' ፀሐፊ ማት ሃንኮክ፤ ተማሪዎች የሞባይል ስልክ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚያግዱ ትምህርት ቤቶችን እንደሚያደንቁ ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ እገዳው ተማሪዎች ዘመናዊ ስልኮችን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እንዳያውቁ ያደርጋቸዋል ሲሉ አንዳንዶች ተቃውመውታል።
የዳሰሳ ጥናቱ እንደሚያስረዳው ዘመናዊ ስልክ ወደ ትምህርት ቤት ይዘውት የሚሄዱት ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በእንግሊዝ በዚህ ዓመት ወደ ትምህርት ቤቶች የተወሰዱ ዘመናዊ ስልኮች በጠቅላላ 2.3 ቢሊየን ፓውንድ እንደሚያወጡ ተቋሙ ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህም በተጨማሪ 43 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት የሚይዙት ስልክ ወላጆቻቸው ከሚይዙት እጅግ የዘመነ ሲሆን በየዓመቱ 13 ቢሊየን ፓውንድ የስልክ ወጭ ክፍያ ይከፈልባቸዋል።
"በየቀኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይዘዋቸው የሚሄዱት ስልኮች ቁጥርም ከአዕምሮ በላይ ነው " ሲሉ በድርጅቱ ውስጥ የሞባይል ስልክ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አርነስት ዶኩ ይናገራሉ።
ሞባይል ልጆቻቸውን ከትምህርት ሊያስተጓጉል እንደሚችል ማንኛውም ወላጅ ሊረዳው የሚችል ነው፤ በመሆኑም ስልኮችን በትምህርት ቤት እንዳይጠቀሙ ማገድ ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም ሲሉ ባለሙያው ያክላሉ።
ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ፤ ማንኛውንም ስልክ መጠቀማቸው አይቀርም በመሆኑም ደህንነታቸው ተጠብቆ ይህንን ክህሎት የሚያዳብሩበት አንዱ ሥፍራ ትምህርት ቤት መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ።
"ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን ደህንነት በማረጋገጥ የአዕምሮ እረፍት ያገኛሉ፤ በስልካቸው ላይ ባለው መተግበሪያ አሊያም በቀጥታ በመደወል የት እንዳሉ ማወቅ ያስችላቸዋል" በማለት ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያይል በምሳሌ ያብራራሉ።
ባለፈው ዓመት የኤተን አስተዳዳሪ፤ ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ከተማሪዎች ስልክ መቀማትን መፍራት የለባቸውም ብለዋል። ነገር ግን በርካቶች በንግግራቸው አልተስማመሙም።
አንዳንዶች እንዲያውም በዚህ ቴክኖሎጂ በተንሰራፋበት ዓለም ህፃናት ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ሊከለከሉ አይገባም ሲሉ ይሟገታሉ።
በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ እና የትምህርት ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ሆዋርድ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ለቢቢሲ "ትምህርት ቤቶችና ትምህርት ለዚህ ዓለም ሕይወት እንድንዘጋጅ የሚረዱን ከሆነ፤ ስልክን መቼ መጠቀም እንዳለብንና እንደሌለብን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው" ብለው ነበር።
"ህፃናት ራሳቸውን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ መማር ይፈልጋሉ፤ ገና በማለዳው ስልካቸውን የሚነጠቁ ከሆነ ግን ይህንን እድል ማግኘት አይችሉም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።















