ፍልስጥኤማዊው ተማሪ 'በማህበራዊ ሚዲያው ባሉ ፅሁፎች' አሜሪካ እንዳይገባ ታገደ

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሲራመዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሃርቫርድ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ችግሩን ለመፍታት እየሞከርኩ ነው ብሏል

ፍልስጥኤማዊው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፤ ጓደኛው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያጋራቸው መረጃዎች አማካኝነት ወደ አሜሪካ እንዳይገባ በባለሥልጣናት መታገዱን አስታውቋል።

ነዋሪነቱ በሊባኖስ የሆነው የ17 ዓመቱ ተማሪ ኢስማኢል አጃዊ፤ ባለፈው አርብ በቦስተን አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ለሰዓታት በጥያቄ እንደተፋጠጠ እና የኢምግሬሽን ባለሥልጣናት ስልኩንና ላፕቶፑን ከፈተሹ በኋላ ቪዛው እንደተሰረዘበት አስረድቷል።

ምንም እንኳን በማህበራዊ ሚዲያ የተላለፉት መረጃዎችን በተመለከተ ምንም የሰራው ወንጀል እንደሌለ በመግለፅ ተቃውሞ ቢያሰማም ከክልከላው ሳያስጥለው ቀርቷል።

የጉምሩክና የድንበር ጠባቂ ቃል አቀባይ ሚካኤል ምካርቲይ እንዳሉት፤ በተማሪው ላይ የተላለፈው ውሳኔ በጉምሩክና ድንበር ጠባቂ መሥሪያ ቤቱ በተደረገው ምርመራ የተገኘን መረጃ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።

ቃል አቀባዩ ሚስጥር መጠበቅ እንዳለባቸው በመግለፅ ምን ዓይነት መረጃ እንደሆነ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ አምርቶ የነበረው ተማሪው ወደ አገሩ ሊባኖን መመለሱም ተገልጿል።

ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም "ችግሩን ለመፍታት ከተማሪው ወላጆችና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየተነጋገርኩ ነው" ብሏል።

ከዚህም ባሻገር ተማሪ ኢስማኢል በአሜሪካ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የሕግ ድጋፍ ተሰጥቶታል።

ባሳለፍነው ሰኔ ወር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ቪዛ የሚጠይቁ አመልካቾች የሚጠቀሙትን ማህበራዊ ሚዲያ ዝርዝር መረጃ እንዲያቀርቡ የሚያዝ ሕግ አውጥቷል።

ሕጉ ተጓዦች የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ ስም፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ የሚጠቀሙበትን የኢሜል አድራሻ እና ስልክ ቁጥራቸውን እንዲያቀርቡ ያዛል።

ሕጉን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ያቀረበው ሲሆን በዓመት 14.7 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ባለሥልጣናት ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።

ይሁን እንጂ ለዲፕሎማሲያዊ ሥራ ቪዛ የሚያመለክቱ ግለሰቦች በዚህ ሕግ ውስጥ እንደማይካተቱ መገለፁ ይታወሳል።