አያቴ ከአምስት የናዚ ግድያ ጣቢያዎች አምልጦ በሕይወት መኖር ችሏል

A photo from Prague in 1945 showing concentration camp survivors

የፎቶው ባለመብት, Lake District Holocaust Project

የቢቢሲዋ ሃና ጌልባርት የአያቷን ታሪክ አስደናቂ ታሪክ እንዲህ ከትባዋለች።

ቤታችን ውስጥ አንድ ጥንታዊ ፎቶ አለ፤ ጥቁርና ነጭ ነው። የትምህርት ቤት ፎቶ ነገር ይመስላል፤ ታዳጊዎች ተደርድረው የተነሱት ፎቶ።

ጊዜው 1945 [እ.አ.አ.] ነው። ፎቶው ላይ የሚታዩት ሕፃናት አይሁዶች ናቸው። ቦታው ደግሞ ፕራግ [የቼክ ሪፐብሊክ የአሁን ዋና ከተማ]። ሕፃናት ፕራግ አካባቢ ከነበረ አንድ የናዚዎች ግድያ ጣቢያ [ኮንሴንትሬሽን ካምፕ] የተረፉ ናቸው።

ብዙዎቹ እርስ በርስ ተቃቅፈዋል። የግማሾቹ ፊት ላይ ፈገግታ ይታያል። ፍፁም ዝምታ የሚነበብባቸው ፊቶችም አልጠፉም።

እኒህ ፊቶች የናዚ ጭፍጨፋን [ሆሎኮስት] በአንዳች ተዓምራዊ አጋጣሚ ያመለጡ ናቸው። ብዙዎቹ ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል፤ ወላጅ አልባ ናቸው።

የመልስ ጉዞ ወደ ፕራግ

The 2019 photo of the family in Prague

የፎቶው ባለመብት, Adrian Pope

ግንቦት፤ 2019 [እ.አ.አ.] ዓመተ ምህረት። ተመሳሳይ ሃውልት ከጀርባቸው ይታያል። ባለነጭ እና ጥቁሩ ፎቶ ላይ ካሉ ሰዎች ጥቂቶቹ ተገኝተዋል። ከባል፣ ሚስትና ልጅ ልጆቻቸው ጋር ነው እዚህ የተገናኙት።

እዚህ የተገኙት አዲስ ፎቶ ለመነሳት ነው። በሕይወት መኖራቸውን የሚዘክር፤ ሞትን ድል መንሳታቸውን የሚያበስር ፎቶ።

ይኼው እኔም እዚህ ታሪካዊ ፎቶ ላይ ልገኝ ሆነ። ሌሎች 12 የቤተሰብ አባላት አብረውኝ አሉ። ነገር ግን ጋዜጠኛም ሆኜ ነው እዚህ የተገኘሁት። ይህንን ታሪክ በብዕሬ ከትቤ ላስቀር።

አያቴ ዳቪድ ኸርማን፤ የሞትን ጭጋጋ ከገፈፉት እኒህ ሕፃናት አንዱ ነው። አምስት የናዚ የግድያ ጣቢያዎች ውስጥ ኖሯል፤ ኦሽዊትዝን ጨምሮ።

ሰቆቃ

Children in a concentration camp

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉዞዬ ከማንቸስተር ይጀምራል። ከተረፉትና አያቴን ከሚያውቁት መካከል ሁለት አሁንም በሕይወት አሉ። ወደቤታቸው በሄድኩ ጊዜ እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉኝ። ሻይ እና ብስኩት ቀርቦልኝ ትንሽ ከተጨዋወትን በኋላ ወደ ቁምነገሬ ገባሁ። ያሳለፋችሁት ሰቆቃ ምን ይመስላል ስል ጠይቅኳቸው። ቤቱ ድንገት ዝምታ ዋጠው።

ከናዚ ሰቆቃ ከተረፈ ሰው ጋር ቁጭ ብዬ ሳወራ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው። ለዚያም ነው አየሩ በዝምታ ሲዋጥ ምን ማለት እንዳለብኝ ጠፍቶኝ እኔም ከንፈሬን ማንቀሳቀስ ያቃተኝ።

ዕድሜዬ 10 እያለ ይመስለኛል ከአያቴ እና ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር ኦሽዊትዝንና ሌሎች 'ካምፖችን' ለመጎብኘት የሄድነው። ሕፃናት የሚላስ ነገር ካልተገዛልን እያሉ ያለቅሳሉ። አስጎብኝው የከተመሩ ጫማዎችና ፀጉሮች አሳየን።

ከአያቴ ወዳጆች ጋር ቁጭ ብዬ ሳወራ ግን ነገሩ ሌላ ሆነብኝ። ወደ ታሪኩ እጅጉን የተጠጋሁ መሰለኝ።

"ሞትን ሁሌም እናየው ነበር"

ሳም ላስኪዬር 91 ዓመታቸው ነው። እጅጌያቸውን ገለጥ አድርገው አንድ ንቅሳት አሳዩኝ። አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ቃለትና ቁጥሮች ይታዩኛል። "ሞትን ሁሌም እናየው ነበር" አሉኝ። "በጢስ ማውጫው በኩል ሲወጣ የሚታየው ጢስ የሰው ነበር። አንድ ሰው ከሶስት ወር የዘለለ አይቆይም፤ እኔ ግን ሰባት ወራት ከረምኩ።

ከመደርደሪያው ላይ አንድ የፎቶ አልበም አንስቶ ያሳየኝ ጀመር። የሆነውን ሲነግረኝ ጠንቀቅ ባለ ሁኔታ ቢሆንም ውስጣቂ ቁስሉ ይገባኝ ነበር። አሁንም ድረስ ስለ ግድያ ጣብያዎቹ እንደሚቃዥ ግን አልደበቀኝም።

ኑሮ በኦሽዊትዝ ካምፕ ውስጥ እንዴት እንደነበረ ሲያጫውተኝ እንዴት አድርጌ ወደ ቃላት እንደምለውጠው ከብዶኝ ነበር። ከሁሉም በላይ ረሃቡን አይረሳውም። ቀጥሎ ስንት ሰዓት ላይ ወይንም በየትኛው ቀን ምግብ እንደሚያገኙ ሳያውቁ መኖር።

አይክ አልተርማን፤ ሌላኛው የ91 ዓት ባለፀጋ የአያቴ ጓደኛና የሰቆቃው ዘመን ተቋዳሽ ናቸው። "ጭንቀታችን የነበረው ቀጣዩ ዳቦ የሚመጣው መቼ ይሆን የሚለው ነው። ረሃብ ደህና አድርጎ አሰቃይቶናል።"

የነፃነት ጣዕም

Wagons full of concentration camp prisoners

የፎቶው ባለመብት, Ike Alterman

አይክ፤ አንድ የፎቶ ድርሳን ከፈቱና ታሪክን ከምስል ጋር እያመዛገቡ ያሳዩኝ ጀመሩ። "አየሽ ይሄን ፎቶ፤ ነፃ መሆናችንን ያወቅን ጊዜ የተነሳ ነው። እንዲጠብቁን የተመደቡት ናዚዎች መጥፋታቸውን ያወቅን ወቅት። ይኸው እኔ፤ እጄን እያልበለብኩ።

በጣም ረጋ ብሎ የሚያወራው አይክ ቀጠለ፤ "በጢስ እንደተበከልን የገባን በሚቀጥለው ቀን ነው። የትም ሊወስዱን አልቻሉም። ሲቀጥል ደግሞ የምንኖርበት ጣብያ ውስጥ የሬሳ ማቃጠያ ነበር።"

ነፃነት. . . የሳም ፊት ፈካ ሲል ታየኝ። "ፕራግ ማለት ለኔ ነፃነት ነች። ነፃ አየር የተነፈስኩት እዚያ ነው።"

ነፃነቱ ከተገኘ በኋላ ሁሉም ፊቱን ወደ ዳቦ አዞረ። ብዙዎች ለዓመታት ረሃብ ውስጥ ነበሩ። በጣም ከመመገባቸው የተነሳ ቁንጣን ይዟቸው ሆስፒታል የገቡ በርካቶች ነበሩ። ጥቂቶች ደግሞ ጨጓራቸው አልፈጭ ብሎ ሞተዋል።

ታሪካዊው ፎቶ ላይ የሚታዩት በርካቶቹ ቴሬዚን [Theresienstadt] በተሰኘው ፕራግ ውስጥ በሚገኝ የግድያ ጣብያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች ያዩትን የሬሣ ብዛት ቆጥረው እንደማይጨርሱት ይናገራሉ።

አሁን ከተማዋ የቱሪስት መናኸሪያ ናት። ላለፉና ለተረፉ እንዲሆን ተብሎ የተሠራ ማስታወሻ የብዙዎች ዓይን ማረፊያ ነው።

Hannah with Arek (left) and Sam (right)
የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲዋ ሃና ከአሬክ [ግራ] እና ሳም [ቀኝ] ጋር

ጉዞ ወደ እንግሊዝ

አያቴን ጨምሮ ሌሎች 732 የሰቆቃው አምላጮች 1945 [እ.አ.አ.] ነበር ወደ እንግሊዝ የመጡት። ከዚያ በኋላ እንደ ወንድም አና እህት ነው የኖሩት። ማንም የላቸውምና።

አዲስ ሕይወት በእንግሊዝ። ከባድ ቢሆንም ተወጥተውታል። ቤተሰብ አፍርተዋል። ልጅ እና የልጅ ልጅ አይተዋል።

ፎቶው ላይ ከሚታዩት በርካታ ሕፃናት መካከል ወንዶች ቢበዙም 83 ሴቶችም ነበሩ።

ስለ ናዚ ጭፍጨፋ [ሆሎኮስት] እንዳውቅ ተደርጌ ነው ያደግኩት። ነገር ግን አያቴና ጓደኞቹ የደረሰባቸው ሰቆቃ 1945 ላይ እንዳላበቃ የገባኝ በቅርቡ ነው።

እናቴ ወጣት እያለች ለአባቷ [አያት] አንድም ቀን ትምህርት ቤት ውስጥ የከፋ ቀን አሳለፍኩ ብላ ነግራው እንደማታውቅ ትነግረኛለች። ሞትን እያሸተቱ ተራን ከመጠበቅ በላይ መቼም የከፋ ቀን የለምና።

David Herman at Buchenwald concentration camp

የፎቶው ባለመብት, Family photo

የምስሉ መግለጫ, ዳቪድ ኸርማን [የሃና አያት] ወደ ቡክሴንቫልት ግድያ ጣብያ በ17 ዓመቱ ነበር የመጣው

የአያቴ ፎቶ አለኝ። ዕድሜው 17 ነበር። ፀጉረን ላጭተውታል። የተቀደደ ፒጃማ አድርጓል። መለያ ቁጥሩም ጎልቶ ይታያል።

ወደ ቡክሴንቫልት ጣቢያ በመጣ ጊዜ የተነሳው ፎቶ ነው። ዓይኖቹ ውስጥ የመኖር ጉጉት ይታየኛል።

እናቴ እንዲህ ትላለች፤ ይህ ወጣት ሰው ማለት ወላጆቹ ተቃጥለው እንዲሞቱ ተፈርዶባቸው እየተነዱ ሲሄዱ ያየ ሰው ነው።