ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ የተገደሉ ባለስልጣናትና ጄኔራሎችን ለመዘከር የሃዘን ቀን አወጀች
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ተሞከረ በተባለው መፈንቅለ መንግሥትና ግድያ ህይወታቸውን ላጡት የክልሉ ባለስልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራሎችን ለመዘከር በመላው አገሪቱ ዛሬ ሰኔ 17 የሃዘን ቀን ሆኖ እንዲውል የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት አውጇል።
የአማራ ክልል መንግሥትም ለተገደሉት ሁለት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሁለቱ ጄኔራሎች ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሃዘን ጊዜ ማወጁ ተሰምቷል።
በአማራ ክልል የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንንና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጡረታ ላይ የነበሩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጄኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው ይታወሳል።
በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተገደሉ ባለስልጣናትና ጄኔራሎችን ሥርዓተ ቀብር የሚያስፈፅም ኮሚቴ መዋቀሩን ትላንትና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።