የተባበሩት መንግስሥታት የትሪፖሊ አየር መንገድ ጥቃትን አወገዘ

ጥቃት የደረሰበት አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት የደረሰበት አየር መንገድ

የተባበሩት መንግሥታት በሊቢያ ውስጥ በስራ ላይ ያለ ብቸኛው አየር ማረፊያ ላይ የተደረገውን የአየር ድብደባ አጥብቆ እንደሚቃወመው አስታወቀ።

ትናንት በሚቲጋ አየር ማረፊያ በተከፈተ ተኩስ ምክንያት ማንኛውም የአየርመንገዱ ስራዎች የተቋረጡ ሲሆን መንገደኞችን በቶሎ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። እስካሁን ግን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ እየተዘገበ ነው።

ጥቃቱን የፈጸሙት በምስራቃዊ ሊቢያ በኩል ዋና ከተማዋን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ያለው የጀነራል ካሊፋ ሃፍታር ወታደሮች ናቸው ሲል የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

የጀነራል ካሊፋ ቃል አቀባይ አውሮፕላኖችና ንጹሃን ዜጎች ኢላማ እንዳልተደረጉ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር የሊቢያ ብሄራዊ ግንባርን የሚመሩ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈውን መንግስት ጠራርጎ በማስወጣት ዋና ከተማዋ ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል።

የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋዬዝ አል ሲራጅ በበኩላቸው ጀነራሉ የመፈንቅለ መንግስት ለማድረግ እየሞከሩ ነው በማለት ከሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሰረት በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ያለውን ተኩስ በመሸሽ ቢያንስ 2800 የሚደርሱ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ሄደዋል።

በሊቢያ የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልእክተኛ ጋሳን ሳላሜ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት የአየር ጥቃቱ ንፁሃን ዜጎች የሚጠቀሙባቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ምንም አይነት እርምጃ ላለመውሰድ የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስና ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የጀነራል ካሊፋ ቃል አቀባይ አህመድ ሚስማሪ በአየር ማረፊያው ቆሞ የነበረ አንድ አውሮፕላን ብቻ የጥቃቱ ኢላማ እንደነበረ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር

የሊቢያ የጤና ሚኒስትር መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው እስካሁን በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች የ25 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 80 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የጀነራል ካሊፋ ሃፍታር ወታደሮች ደግሞ 19 ተዋጊዎቻቸውን እንዳጡ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው እሁድ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት ለሁለት ሰአታት የቆየ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ሲሆን ንጹሃን ዜጎችን ከአካባቢው ለማስወጣት የተደረገ ሙከራ ነበር።

የትሪፖሊ ነዋሪዎችም ከባድ ጦርነት እነደሚመጣ በመገመት ምግብና ነዳጅ ከአሁኑ ማጠራቀም እየጀመሩ ነው።