የልጇን ልጅ የወለደችው አያት

የፎቶው ባለመብት, Ariel Panowicz / www.arielpanowicz.com
የ61 ዓመቷ አሜሪካዊቷ አያት፣ ወ/ሮ ሲሲሊ፣ ልጇ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ቢሆንም ከትዳር አጋሩ ጋር የራሳቸውን ቤተሰብ ለመመስረት ያላቸውን ፍላጎትና ወልደው ለመሳም ያላቸውን ጉጉት ትሰማለች።
ይኼኔ ለሁለቱ ጥንዶች ሀሳብ የነበረውን ማህፀን የማግኘት ሀሳብ እርሷ ማህፀኗን ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆኗ ተቃለለ።
ከዚያም ልጇን ሴት ልጅ ወልዳ አስታቅፋዋለች።
ነገሩ ትንሽ ግራ ገብ ይመስላል።
ወ/ሮ ሲሲሊ ኤሌጅ ወንድ ልጇ ከተመሳሳይ ፆታ የትዳር አጋሩ ጋር ትዳር የመሰረተ ሲሆን ልጅ የማግኘት ተስፋው የመነመነ በነበረበት ጊዜ ነበር ማህፀኗን ሰጥታ ሴት ልጅ የወለደችላቸው።
መጀመሪያ ወ/ሮ ሲሲሊ ይህን ሃሳብ ያነሳችው ልጇና ባለቤቱ ቤተሰብ ለመመስረት ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት ሲነግሯት ነበር። ሃሳብዋንም ስታጋራቸው ሁለቱም እንደሳቁባት ታስታውሳለች።
"እስከ ረጅም ጊዜ ሃሳቡ ቀልድ ተደርጎ እንጂ እውን ይሆናል ብለን በውል አንነጋገርበትም ነበር" ትላለች ወ/ሮ ሲሲሊ።

የፎቶው ባለመብት, Ariel Panowicz / www.arielpanowicz.com
ነገር ግን በጊዜ ሂደት ልጇ ማቲው ኤሌጅና ባለቤቱ ልጅ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ በህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ሲፈልጉ ስለነበር የእናቱ ማህፀን ምቹ መፍትሄ እንደሆነ ተረዱ።
በዚህም መሰረት ወ/ሮ ሲሲሊ ቃለመጠይቅና ብዙ የጤና ምርመራ ያደረገች ሲሆን ውጤቶቹም ህልማቸውን የሚያሳካ ሆኑ።
ወ/ሮ ሲሲሊ ስለ ምርመራው ስትናገር "በጤናዬ ዙሪያ በጣም ጠንቃቃ ነኝ፤ ፅንስ መሸከም እችላለሁ ብዬ አልተጠራጠርኩም ነበር" ትላለች።
እናቱ ማህፀን መስጠት እንደምትችል ከተረጋገጠ በኋላ የልጇ ዘር ተወስዶ የሴቴ እንቁላል ደግሞ ከባለቤቱ አቶ ዶፈርቲ እህት በመውሰድ ልጅ የማግኘት ህልማቸው ተጀመረ።
የማቲው አባት "ሁልጊዜም ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥተን መፍትሄዎችን መፈለግ እንዳለብን እናውቅ ነበር" ይላሉ።
ወ/ሮ ሲሲሊ እርግዝናው ሙሉ በሙሉ ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳለፈ ስትናገር "ከበፊቶቹ እርግዝናዬ ግን ትንሽ ከበድ ይላል" ብላለች።
የልጇ ባለቤት ዶፈርቲ ድርጊቷን " በጣም በፍቅር የተሞላ" ብሎ ሲገልፀው አያትየውንም "ለራሷ የማትል ሴት ናት" ብሏል።
እርግዝናዋ ለሌሎቹ ሁለት ልጆችዋ በመጀመሪያ "አስደንጋጭ" ቢሆንም ከተነገራቸው በኋላ ሁለቱም በሁኔታው ደስተኛ ነበሩ።
ወ/ሮ ሲሲሊ በእርግዝናዋ ወቅት ከመድን ዋስትና ድርጅቷ ጋር ችግር እንደገጠማት ትናገራለች። የመድን ድርጅቱ የራስዋ ልጅ ቢሆን የሚሸፍናቸውን ወጪዎች የራሷ አይደለም በማለት ድጋፍ ከማድረግ ተቆጥቧል።

የፎቶው ባለመብት, Ariel Panowicz / www.arielpanowicz.com
የማቲው አባት በባለቤታቸው ድርጊት ላይ "እነዚህ ዓይነት ጥቃቅን ነገሮች በመንገዳችን እንቅፋት ሆነውብናል" ይላሉ።
በመቀጠልም " የሚገጥሙንን ተቃውሞዎች የግል ጉዳይ አድርጎ መውሰድ ትቻለሁ፤ዋናው ነገር ቤተሰብ፣ ጓደኞችና የሚደግፉን ብዙ ሰዎች አሉ" ሲሉ ይናገራሉ።
ልጅቱ ከተወለደች አንድ ሳምንት በኋላ ሁለቱም አያትና የልጅ ልጅ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።
"ይች ሕፃን በፍቅርና በሚደግፋት ቤተሰብ ውስጥ ነው የምታድገው" ብለዋል አራሷ ወ/ሮ ሲሲሊ።















