ወንዶች ከሴቶች በበለጠ ለምን እራሳቸውን ያጠፋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለጭንቀትና እራስን ለማጥፋት ተጋላጭ ናቸው። ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ለምን እራሳቸውን በማጥፋት ወንዶች ከሴቶች በብዙ ዕጥፍ ይበልጣሉ?
እራስን ማጥፋት አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት በጣም ጥቂት አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ 2016 (እ.አ.አ) 793 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እራሳቸውን አጥፍተዋል። ብዙዎቹ ደግሞ ወንዶች ነበሩ።
እራስን ማጥፋት በጣም የተወሳሰበ ምክንያት ያለው ሲሆን በባህሪው ደግሞ በእርግጠኝነት የሞቱን ምክንያት እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር የያስቸግራል።
ስለ አዕምሮ ጤንነት የሰዎች እውቀት እያደገ ባለበት ሁኔታ ብዙዎች እራሳቸውን ለማጥፋት የሚየበቁ የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ። እስካሁን ግን መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ አሃዙ ከሁለቱ ፆታዎች አንጻር ያለው ሰፊ ልዩነት ነው።
ልዩነቱን ይበልጥ የሚያሰፋው ደግሞ ሴቶች ለጭንቀት ከወንዶች በላይ ተጋላጭ መሆናቸው ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች ከወንዶች በላይ እራሳቸውን ለማጥፋት ይሞክራሉ። ነገር ግን የወንዶች እራሳቸውን የሚያጠፉበት መንገድ ጭካኔ የተሞላበት ስለሆነ ሰዎች እርዳታ ከመድረሱ በፊት ህይወታቸው ያልፋል።
ወንዶች እራስን በማጥፋት ለምን ይሰቃያሉ? መፍትሄውስ ምንድን ነው?
ለወንዶች እራስን ማጥፋት ምክንያቶች
ዋናው ቁልፍ ምክንያት የወንዶች የውስጣቸውን ስሜት ለመግለፅ መቸገራቸው ነው። ሴቶች ችግራቸውን በቀላሉ የማካፈልና የመናገር ባህሪ ሲኖራቸው ወንዶች ግን ለብቻቸው በውስጣቸው መያዝን ይመርጣሉ።
ለዓመታት የብዙ ማህበረሰቦች አመለካከት ወንዶች 'ጠንካራ' እንዲሆኑና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች አምነው እንዳይቀበሉና እርዳታ እንዳይሹ አድጓቸዋል።
ይህ የወንዶች ባህሪ ከልጅነት ጊዜ ይጀምራል። "ወንድ ልጆችን 'ወንድ ልጅ አያለቅስም' እያልን ገና በለጋ እድሜያቸው ስሜታቸውን እንዳያካፍሉ እናደርጋቸዋልን። ምክንያቱ ደግሞ ስሜትን ማጋራት 'ልፍስፍስ' መሆን መገለጫ አድርገን መውሰዳችን ነው" በማለት የማህበረሰቡን ተፅዕኖ ኮልማን ኦ ድሪሰኮል የላይፍላይን ሃላፊ ትናገራለች።
"ወንዶች ስለ አዕምሮ ጤናቸው የህክምና ባለሙያን የማማከር ልምዳቸው አነስተኛ ነው። ይህ ግን ወንዶች እንደሴቶች ተመሳሳይ ችግር ስለሌላቸው አይደለም። ይልቁንም ወንዶች እራሳቸውን እስከ ማጥፋት ሊያበቋቸው የሚችሉትን እያስጨነቋቸው ያሉ ነገሮችን ለይተው ለማወቅ መቸገራቸው ነው" በማለት ሃርካቪ ፍሬደማን በአሜሪካ እራስን ማጥፋት የሚከላከል ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ይናገራሉ።
አንዳንድ ወንዶች የህክምና አገልግሎት ከመሻት ይልቅ አደገኛ በሆነ መልኩ እራሳቸውን ለማከም ይሞክራሉ።
"ዕፆችን የመጠቀምና አልኮልን የማዘውተር ባህሪ በወንዶች ዘንድ ከፍተኛ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ያሉበትን የጭንቀት ስሜት ያንፀባርቃል። እራስን ለማጥፋት ያለውን እድልም ያመለክታል" ሲሉ ሃርካቪ ፍሬድማን የጨምራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌሎች እራስን ለማጥፋት ሊያጋልጡ የሚችሉ መንስኤዎች ደግሞ ከቤተሰብና ከሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ናቸው። ከኢኮኖሚ መውደቅ እና ከሥራ አጥነት ጋር በተያያዘ እራስን የማጥፋት አጋጣሚም ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ከኢኮኖሚ መሽቆልቆሉ በኋላ ባሉት 18 እስከ 24 ወራት ውስጥ ጎልቶ ይታያል።
እ.አ.አ 2015 ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በእያንዳንዱ ሥራ አጥነት ላይ ለሚታይ የ1 በመቶ ጭማሪ፤ እራስን ማጥፋት በ0.79 በመቶ በሚሆን መጠን ከፍ ይላል።
ስለ ገቢ መጨነቅና ሥራ ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ የማንኛውንም ሰው የአዕምሮ ጤንነትን ይጎዳል። ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ የማህበረሰብ ተፅዕኖና የማንነት ቀውስ ምክንያቶች ናቸው።
"የምናድገው እራሳችንን ከሌሎች ሰዎች ጋር እያነፃፀርን በገቢ ደግሞ ስኬታማ እንድንሆን ነው። በዚህ ምክንያት ከገቢ አንፃር የማንቆጣጠራቸው ችግሮች ሲያጋጥሙን በጣም ይከብደናል" ይላሉ ሲሞን ገኒንግ።
ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ብቸኝነት ነው።
ከራስ ውጭ የሆኑ ክስተቶች እራስን ወደማጥፋት እየተቃረበ ያለን ሰው ሁኔታን ሊያባብሱ ቢችሉም መቼም ቢሆን ግን ብቸኛው ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም።
"በጣም ብዙ ሰዎች ሥራቸውን ያጣሉ፣ ሁላችንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከምንወዳቸው ጋር ያለንን ግንኙነት አጥተናል፤ ነገር ግን እራሳችንን አናጠፋም" ሲሉ ሃርካቪ ፈሬድማን ይናገራሉ።
መፍትሄዎች
እራስን ማጥፋትን ለመሰለ የተወሳሰበ ሁኔታ ቀጥተኛ መልስ ማግኘት አይቻልም። ነገር ግን የተለያዩ መድረኮች፣ ፖሊሲዎች እና አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለመፍትሄዎች በር እየከፈቱ ነው።
ባጠቃላይ ትኩረት እየተደረገበት ያለው "ለወንዶች ስሜታቸውን ማካፈል ምንም ማለት እንዳልሆነና ሲያካፍሉም እንደ ጥንካሬ እንዲወሰድ ማድረግ ላይ ነው" ይላሉ ኦ ድሪስኮል።
ጎን ለጎን ቴክኖሎጂ ሌሎች አማራጮችንም እያቀረበ ነው። ሁሉም ሰው የውስጡን ለሌላ ሰው ለመናገር ላይፈልግ ይችላል። ለዚህም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እርዳታ የሚሻ ሰውን በማነጋገር የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዲያገኙ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ሌላኛው መፍትሄ ደግሞ እራስን ማጥፋት በቤተሰብ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ሰዎች እንዲገነዘቡ ማድረግ ነው። ይህ በአንዳንድ ወንዶች "እራሱን ማጥፋቱ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" የሚለውን ሃሳብ ለመግታት ይረዳል ይላሉ ገኒንግ።
















