ከጄሰን ድሩሎ ጀርባ ያሉት ኢትዯጵያውያን ተወዛዋዦች

የኢትዮጵያዊነት ቡድን አባላት

የፎቶው ባለመብት, BOLEWOOD STUDIO

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያዊነት ቡድን አባላት

አሜሪካዊው ድምጻዊ ጄሰን ድሩሎ ከቻይናዊው አቀንቃኝ 'ላይ' እንዲሁም ከኮርያዊያኑ 'ኤንሲቲ 127' ጋር በጥምረት ያወጣው ዘፈን ባለፉት ስድስት ቀናት ብቻ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።

"ሌትስ ሸት አፕ ኤንድ ዳንስ" የሙዚቃው መጠሪያ ነው። "እስኪ ሌላ ሌላውን ትተን፣ ዝም ብለን እንደንስ" እንደማለት ነው።

የሙዚቃው ቪድዮ ላይ በዳንስ ብቃቱ የገነነው ጄሰን ድሩሎ ሲወዛወዝ ይታያል። ጃፓናዊያኑ ኤንሲቲ 127ቶችም ይውረገረጋሉ።

የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሳቡት ግን በቪድዮው ላይ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ተወዛዋዦች ናቸው።

የሙዚቃ ቪድዮው ሲጀምር የፑል መጫወቻ ጠረጴዛ ላይ የሚደንስ ኢትዮጵያዊ ህጻን ይታያል። ከዚያም በስኬት ቦርድ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች።

ጄሰን ድሩሎ በሙዚቃው እኩሌታ ላይ "ኢትዮጵያውያን ሴቶች እስኪ ትከሻችሁን አሳዩኝ?" በሚል መልክ ኢትዮጵያዊያን እንዲወዛወዙ የሚጠይቅ ስንኝ አለው።

ኢትዮጵያውያኑ ተወዛዋዦችም እስክስታውን ይወርዱታል።

ለንደን፣ ሎስ አንጀለስ፣ ጃማይካ፣ እስያ. . . ሙዚቃው የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን ውዝዋዜ ያሳያል።

"ኢትዮጵያዊነት"

"ኢትዮጵያዊነት" በወጣት ተወዛዋዦች የተመሰረተ የባህላዊ ውዝዋዜ ቡድን ነው። የቡድኑ አባላት ባህላዊ ውዝዋዜን ከዘመነኛ ዳንስ ጋር በማዋሀድ ይታወቃሉ።

በርካታ የሙዚቃ ቪድዮዎች ላይ የሚወዛወዙት ወጣቶች፣ በጄሰን ድሩሎ የሙዚቃ ቪድዮ ላይም ተሳትፈዋል።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት "ኢትዮጵያዊነት"ን የመሰረቱት ስድስት ወጣቶች ዛሬ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ቪድዮ ላይ ችሎታቸውን ማሳየት ችለዋል።

ተወዛዋዦቹ 'ባላገሩ አይዶል' የተሰኘውን ውድድር በውዝዋዜ ዘርፍ ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያዊነቶች በጄሰን ድሩሎ የሙዚቃ ቪድዮ ላይ የተሳተፉት የቪድዮው አዘጋጆችን ጥሪ ተከትለው እንደሆነ ከቡድኑ አባላት አንዱ የሆነው ፍቅረማርያም በቀለ ይናገራል።

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ ዳንሰኞች ሥራቸውን የሚያሳይ ቪድዮ ለአዘጋጆቹ ካሳዩ በኋላ "ኢትዮጵያዊነት" ተመርጧል።

"ልምምድ የምናደርግበት ቦታ መጥተው ቪድዮ ሲቀርጹን በጣም ወደውን ነበር። ይህን ቪድዮ ዓለም ነው የሚያየው። ድሮ የምንሰራው ቪድዮ ግን ሀገር ውስጥ የተገደበ ነበር። እኛ ከምንም በላይ የምንፈልገው ኢትዮጵያዊ ባህላችን ዓለም ላይ ከፍ እንዲል ነው።"

ተወዛዋዦቹ ከዚህ ቀደም ከሠሩባቸው የሙዚቃ ቪድዮዎች የቤቲ ጂ፣ የፍቅረአዲስ ነቃጥበብና የዮሴፍ ገብሬን መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያዊነቶች በውዝዋዜ መላው ሀገሪቱን እንደሚወክሉ ለማሳየት የቡድናቸውን መጠሪያ መምረጣቸውን ፍቅረማሪያም ይናገራል።

ፍቅረማሪያም የሙዚቃ ቪድዮው ኢትዮጵያን እንዲሁም ባህሏን እንደሚያስተዋውቅ ያስረዳል።

"ውዝዋዜ ቋንቋ ነው" የሚለው ፍቅረማሪያም ተወዛዋዦችን እንደ ባህል አምባሳደር ያያቸዋል። እንደ ጄሰን ድሩሎ ባሉ እውቅ ሙዚቀኞች ቪድዮ ክሊፕ ላይ መታየት የተወዛዋዦቹን እውቅና እንደሚያሳድገው ያምናል።

የሙዚቃ ቪድዮው አዘጋጆች የቡድኑን ስድስት አባላትና ኬንያዊያን ተወዛዋዦችን ይዘው ወደ ሐረር ካቀኑ በኋላ ነበር ቪድዮው የተቀረጸው።

ቪድዮውን ቀርጾ ለማጠናቀቅ አራት ቀን ወስዶባቸዋል። ቪድዮው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልታወቁ ባህሎችን ቀንጭቦም ቢሆን እንደሚያሳይ ተወዛዋዡ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ውዝዋዜ ከማጀቢያነት ባለፈ ራሱን እንደቻለ ጥበብ እንደማይታይ የሚናገረው ፍቅረማሪያም፤ ተወዛዋዦቹ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ መታየታቸው የተዛባውን አመለካካት በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፈው ተስፋ ያደርጋል።