የእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የረሃብ ሚኒስቴር ይሾምልን እያሉ ነው

ባዶ ሰሃን የያዘ ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥቂት የማይባሉ የእንግሊዝ ፓርላማ አባላት በሃገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የምግብ እጥረት የሚከታተልና በተለይም ህጻናት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሚኒስትር መስሪያ ቤት እንዲቋቋም አንፈልጋለን ብለዋል።

በፓርላማው የአካባቢ ጉዳዮች ኦዲት ኮሚቴ እንደገለጸው 19 በመቶ የሚሆኑት ከ15 ዓመት በታች እንግሊዛውያን ህጻናት ምግብ ለመግዛት እጅግ ከሚቸገሩ ቤተሰቦች ጋር ነው የሚኖሩት። ይህ ቁጥር ደግሞ በአውሮፓ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ኮሚቴው እንደሚለው በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ ሚኒስትሮች ችግሩን ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት አልቻሉም። የእንግሊዝ መንግሥት ግን ስራ ከሌላቸው ቤተሰቦች ጋር የሚኖሩ ህጻናት ቁጥር ከሌላ ጊዜው በተለየ ዝቅተኛ ነው ሲል ይከራከራል።

እንግሊዝ ውስጥ የተመጣጠኑና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙ ምግቦችን መግዛት የማይችሉ ዜጎች ቁጥር በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ እንደመጣ የፓርላማ አባላቱ የጠቆሙ ሲሆን ስራ አጥ የሆኑትና ህጻናት ደግሞ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ናቸው ብለዋል።

አባላቱ እንዳሉትም ዋነኛ ሃላፊነቱ ረሃብና የምግብ እጥረትን መከታተል የሆነ ሚኒስትር መስሪያ ቤት በአፋጣኝ ሊቋቋም ይገባል።

የረሃብና ምግብ እጥረት መንስኤዎች፣ መጠን፣ የሚያስከትሉትን ጉዳትና የመከላያ መፍትሄዎች ማቅረብ ደግሞ ዋነኛ የስራ አትኩሮቱ አድርጎ መስራት አለበት ብለዋል።