የአገልግል ምግብ አምሮዎታል?

ምግብ በአገልግል ያደርሳሉ

የፎቶው ባለመብት, BISRAT BELAYNEH

የምስሉ መግለጫ, ምግብ በአገልግል ያደርሳሉ

አገልግል ሲባል ወደ ብዙዎች ህሊና የሚመጣው ለረዥም ጉዞ የተሰነቀ ጥኡም ምግብና በዛፍ ጥላ ተከልሎ ማዕዱን መቋደስ ነው።

ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ከከተማ ወጥቶ ለመዝናናት ሲታሰብ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ ብሎ በተፈለገው ቀን፣ ለተፈለገው መሰናዶ ምግብ ማዘጋጀትም የተለመደ ነው።

ቤላ-ዶና የተባለ የምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ ተቋም፤ አገልግል ቤት ውስጥ የማሰናዳትን ልማድ 'አዘምኖ'፤ "እናንተ ስለምትሄዱበት ቦታ ብቻ አስቡ፤ የምግብ ዝግጅቱን ለኛ ተውት" እያለ ነው።

በስራ በመወጠር አልያም በሌላ ምክንያት ጊዜ ያጡ ግለሰቦችን ታሳቢ በማድረግ የተጀመረ አገልግሎት ነው።

ለቅሶ ለመድረስ፣ ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ለሌላ ጉዳይም ምግብ የሚያሰናዱ ተቋሞችን መቅጠር እየተለመደ መጥቷል።

ለምግብ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ለመስተንግዶም ተቋም መቅጠር የሚሹ ግለሰቦች መብዛታቸው ደግሞ ነጋዴዎችን ወደ ዘርፉ እየሳበ ነው።

በቀን ከ15 እስከ 50 ትእዛዝ ይቀበላሉ

የፎቶው ባለመብት, BISRAT BELAYNEH

የምስሉ መግለጫ, በቀን ከ15 እስከ 50 ትእዛዝ ይቀበላሉ

በዘርፉ አዋጭነት ከተሳቡ አንዱ ብስራት በላይነህ ነው። የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ነው። የመኪና ኪራይ፣ የኤሌክትሮኒክስ ሽያጭ፣ የቴሌቭዥንና ሬድዮ ማስታወቂያ ይሰራ ነበር። አሁን ግን አትራፊ ወዳለው የምግብ ዝግጅትና አቅርቦት ገብቶ ቤላ-ዶናን አቋቁሟል።

መነሻ ያደረገው ምሳ ቋጥሮ መሸጥን ነበር።

ቤታቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ ወይም ፍላጎቱ ለሌላቸው ሰዎች ቢሯቸው ድረስ ምሳ ቋጥሮ መላክ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል።

ምሳ ሰአት ላይ፤ ምግብ በምሳ እቃ እንዲላክላቸው የሚፈልጉ ሰራተኞች የሚጠበቅባቸው ስልከ መደወል ብቻ ነው። የሚፈልጉትን የምግብ አይነት ያዛሉ። ከዛም ምሳ ሰአት ላይ ትኩስ ምግብ ይወሰድላቸዋል።

"ለደንበኞቻችን ትኩስ ምግብ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ያሉበት ቦታ ድረስ ለማቅረብ አስበን ነው ስራውን የጀመርነው" ይላል።

ንግዱ እየተጧጧፈ ሲመጣ ምግብ በአገልግል ወደ ማድረስ ተሸጋገረ።

ምግቡ የሚዘጋጀው አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው። በምሳ እቃ ሀያ ሁለት፣ ቦሌ፣ መርካቶ፣ አውቶብስ ተራ፣ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢም ይደርሳል። በአገልግል ሲሆን ግን የሰፈሮች ድንበር አይገድበውም።

"ሽሮም፣ ዶሮም አለን"

ብስራት ምግብ በአገልግል ወደማቅረቡ ስራ የገባው በምግብ ዝግጅት ከሰለጠነች ዘመዱ ጋር ነበር። የሚኖሩበት ቤት ውስጥ ምግብ በማዘጋጀት ከጀመሩ በኃላ ስራው ሲሰፋ ተጨማሪ ምግብ አብሳዮች ቀጠሩ።

የጸምና የፍስክ ምግብ ያቀርባሉ

የፎቶው ባለመብት, BISRAT BELAYNEH

የምስሉ መግለጫ, የጸምና የፍስክ ምግብ ያቀርባሉ

ምግብ መሰናዶውን በአንድ በኩል ሲያካሂዱ፤ ተረክበው በየአስፈላጊው ቦታ የሚያደርሱ ተቀጣሪዎችም አሏቸው።

ስለ አገልግሎታቸው የሚያስተዋውቁት በፌስቡክ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሚዲያ ያልደረሷቸውን ደግሞ በያሉበት በመሄድ በራሪ ወረቀት ይበትናሉ።

ንግዱ በዋነኛነት የሚካሄደው በቢሮዎችና ሱቆች ስለሆነ በነዚህ አካባቢዎች ራሳቸውን ከማስተዋወቅ አይቦዝኑም።

በቀን ከ 15 እስከ 50 ትእዛዝ ይቀበላሉ። የምግብ ዝርዝሩ የጾምና የፍስክ፤ የሀገር ውስጥና የባህር ማዶ በሚል ተከፍሏል።

ክትፎ፣ ጥብስ ፍርፍር፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ. . . ዝርዝሩ ሰፊ ነው።

ሽሮና ፓስታን የመሰሉ ምግቦች በምሳ እቃ ከ 40 እስከ 45 ብር ይሸጣሉ። ክትፎ ደግሞ በ85 ብር። በአገልግል ሲሆን፤ ሰባት የጾም ምግቦች ተካተው 73 ብር ያስከፍላል። ለአምስት አይነት የፍስክ ምግብ 85 ብር ይከፈላል።

ወደድ የሚለው በብዙዎች የሚወደደው ዶሮ ነው። ሙሉ ዶሮ ወጥ፣ ከአይብና ከ 12 እንቁላል ጋር 900 ብር ነው።

"ሰዎች 'የቤት የቤት የሚል ምግብ ነው' ይሉናል'" የሚለው ብስራት በተለይም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ታሳቢ ማድረጋቸውን ይገልጻል።

"ወደ አስቤዛ ሸመታ መግባት እንፈልጋለን"

'ዘመነኛ' የሚባለው ኑሮ ቤት ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ምግቦችን ወደ ተቋም እያዘዋወረ ይመስላል። ብስራትም የማህበረሰቡን ፍላጎት ተንተርሶ የቅመማ ቅመም ዝግጅትና የአስቤዛ ሸመታ ውስጥም ለመግባት አስቧል።

ምግብ በምሳ እቃ ያደርሳሉ

የፎቶው ባለመብት, BISRAT BELAYNEH

የምስሉ መግለጫ, ምግብ በምሳ እቃ ያደርሳሉ

"ግባችን የሰውን ህይወት ማቅለል ነው" ይላል።

ስራውን ሲጀምሩ ብዙ ሰው እውን በአገልግል ያመጣሉ? ብሎ ይጠራጠር ነበር። አሁን ግን ተአማኒነት እያገኙ እንደሆነ ያምናል።

"በብዙ ቦታዎች አገልግል አልተተወም፤ ምናልባት የዘነጉት ወጣቶች ካሉ እያስታወስናቸው እንደሆነ ይሰማኛል" ይላል። በጊዜ ሂደት የአስቤዛ ሸመታን እንደሚያስለምዱም ያምናል።