አሜሪካ የመናዊቷ እናት በሞት አፋፍ ላይ ያለ ልጇን እንዳታይ ከለከለች

ህፃኑ እንደማይተርፍ ዶክተሮች ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, ህፃኑ እንደማይተርፍ ዶክተሮች ተናግረዋል

የመናዊቷ እናት በካሊፎርኒያ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኝ ህፃን ልጇን ለማየት ወደ አሜሪካ እንዳትገባ ተከለከለች።

የሁለት ዓመቱ ህፃን አብዱላህ ሃሰን የተወለደው ከአእምሮ ህመም ጋር ሲሆን ህይወቱን ማትረፍ እንደማይቻል ዶክተሮች ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የህፃኑ እስትንፋስ ያለው በህክምና መሳሪያ ድጋፍ ሲሆን መሳሪያው ተነስቶ እስትንፋሱ እንዲቋረጥ ከመደረጉ በፊት እናቱ ለመጨረሻ ጊዜ ልታየው መፈለጓን ቤተ ዘመዶች ገልፀዋል።

የህፃኑ እናት ልጇን ማየት ያልቻለችው የትራምፕ አስተዳደር በጣለው የጉዞ እገዳ ምክንያት እንደሆነ ቤተ ዘመዶቹ ጨምረው ገልፀዋል።

ህፃኑ አብዱላህ እና አባቱ የተወለዱት አሜሪካ ውስጥ በመሆኑ የአሜሪካ ዜግነት አላቸው።

የህፃኑ እናት በአሁኑ ወቅት የምትገኘው ግብፅ ሲሆን ህፃኑን እናቱ እንድታየው ወደ ግብፅ እንውሰደው ቢባል በጉዞው ሊሞት ስለሚችል ይህ የሚታሰብ እንዳልሆነ ተገልጿል።

አባት ልጁን ለህክምና ወደ አሜሪካ ይዞት የሄደው ከሶስት ወራት በፊት የነበረ ሲሆን እናትም እንደ አስፈላጊነቱ ትከተለናለች በሚል እሳቤ ነበር።

ነገር ግን ዶክተሮች የህፃኑ ህመም እጅግ ፅኑ መሆኑን ሲገልፁ እናት የግድ ከልጇ ጎን መሆን እንዳለባት በማመን ለቪዛ ማመልከቻ አስገቡ።

ከአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የደረሳቸው መልስ ግን እናት ቪዛ መከልከሏን የሚገልፅ ነበር።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ለቢቢሲ እንደገለፁት እናት በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ እንድትገባ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

"እናቱ የምትፈልገው ለመጨረሻ ጊዜ የልጃችንን እጅ መያዝ ነው" በማለት የ22 ዓመቱ የህፃኑ አባት አሊ ሃሳሳን ተናግሯል።

የትራምፕ አስተዳደር ስራ እንደጀመረ በአብዛኞቹ የሙስሊም አገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው። በዘህም የሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሆኗል።