በህንድ ደልሂ ግዛት የተደፈረችው ህፃን በአስጊ የጤንነት ሁኔታ ትገኛለች

በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን በመቃወም የተደረገ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በህንድ ደልሂ ግዛት የ3 ዓመቷ ህፃን በጎረቤቷ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ከተፈፀመባት በኋላ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተገለፀ።

ጥቃቱን ፈፅሟል የተባለውና በቁጥጥር ስር የዋለው የ40 ዓመቱ ተጠርጣሪ የፀጥታ አስከባሪ ሲሆን ህፃናት በሚኖሩበት ህንፃ ተቀጥሮ ይሰራ ነበር።

በወቅቱ ፖሊስ ራሷን ስታ ያገኛት ሲሆን በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ አስፈላጊው ህክምና እየተደረገላት ይገኛል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጣን በቀሰቀሰውና ከዚህ ቀደም በአውቶብስ ውስጥ በቡድን የተደፈረችዋን ተማሪ ስድስተኛ ዓመት ዝክር ወቅት ድርጊቱ እንደተፈፀመ በደልሂ የሴቶች ኮሚሽነር ስዋቲ ማሊዋል ገልፀዋል።

እስካሁን ድረስ ህፃኗ ከጉዳቷ ልታገግም መቻል አለመቻሏን በተመለከተ ግልፅ የሆነ መረጃ ባይኖርም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው ሲሉ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ተጠርጣሪው ጥቃቱን ሲፈፅም በቀን ስራ የሚተዳደሩት የህፃኗ ቤተሰቦች ለስራ ወጥተው ነበር፤ ከዚያም ህፃኗን ከረሜላ በመስጠት ከቤት ይዟት እንደወጣ ታውቋል።

ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተረጋገጠ እስከሞት የሚደርስ ቅጣት ሊያስቀጣው እንደሚችል ፖሊስ አስታውቋል።

በህንድ በዚህ ዓመት ብቻ በህፃናት ላይ በተከታታይ የደረሱ ጥቃቶችን ተከትሎ አዲስ ቁጣ ቀስቅሷል፤ ባለፈው ሚያዚያ ወር አንዲት የስምንት ዓመት ህፃን በቡድን የመድፈር ጥቃት ተፈፅሞባታል፤ ባለፈው ሰኔ ወርም እንዲሁ የ7 ዓመት ህፃን ልጂ መደፈሯን ተከትሎ በማዕከላዊ ህንድ ግዛት ማዲህያ ፓራደሽ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል።

በህንድ የሚፈፀም ጥቃት

የህንድ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) መረጃ መሰረት

  • ዕድሜዋ ከ 16 ዓመት በታች የሆነ አንዲት ህፃን በእያንዳንዱ 155 ደቂቃዎች ስትደፈር፤ ከ10 ዓመት በታች የሆነች ህፃን በእያንዳንዱ 13 ሰዓታት ትደፈራለች።
  • በህንድ የሚደፈሩ ህፃናት ሪፖርት እንደሚያሳየው ከ6 ዓመታት በፊት የነበረው 8 ሺህ 541 ቁጥር ጨምሮ ከሁለት ዓመታት በፊት 19 ሺህ 765 ደርሷል።
  • ከሶስት ዓመታት በፊት ከ10 ሺህ የሚበልጡ ህፃናት ተደፍረዋል።
  • በህንድ የሚኖሩ 240 ሚሊዮን ሴቶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ።
  • መንግስት በሰራው አንድ ጥናት 53 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት ወሲባዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል።
  • 50 በመቶ የሚሆኑት ጥቃት አድራⶄች ደግሞ የቅርብ ሰዎችና እንክብካቤ አድራጊዎች ናቸው።