በጥሞና ላይ የነበሩት የቡድሂስት መነኩሴ በአቦሸማኔ ተገደሉ

በህንዷ ግዛት ማሀራሽትራ በጥሞና ላይ የነበሩት መነኩሴ በአቦሸማኔ እንደተገደሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ገለፁ።

ለነብሮች ተከልሎ በሚገኘው ታቦዳ ጫካ ውስጥ ራሁል ዋልኬ የተሰኙት መነኩሴ በጥሞና ላይ እንደነበሩ መገደላቸውን ፒቲአይ የተባለው የዜና ወኪል ለባለስልጣናቱ ገልጿል።

በጫካው አካባቢ በሚገኘው የቡድሂስት ቤተመቅደስ ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት ራሁል ለጥሞና በሚል ወደ ጫካው ራቅ ብሎ እንደገቡ ዘገባዎች ጠቁመዋል።

በአካባቢው በጥበቃ ስራ የተሰማሩ ሰዎች መነኩሴው ከአካባቢው ራቅ ብሎ እንዳይሄዱ አስጠንቅቀውት እንደነበረም ገልፀዋል።

ነገር ግን መነኩሴውን የገደለው አቦሸማኔ ለመያዝ እቅድ እንደተነደፈም የአካባቢው የጥበቃ ባለስልጣን የሆኑት ጂፒ ናራዋኒ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይህንንም ለማከናወን ሁለት ዋሻዎችን ያዘጋጁ ሲሆን ወጥመድና ማደንዘዣንም ጨምረው እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

የመንግሥት ባለስልጣናት ጨምረው እንዳሳወቁት ለሟቹ መነኩሴ ካሳ የሚሆንም 1.2 ሚሊዮን ሩፒ ወይም 16 ሺ ስምንት መቶ ዶላር ለቤተሰቦቹ ይከፈላቸዋል።

በዚሁ ቤተመቅደስ የሚያገለግሉት ሌላኛው መነኩሴ ጥቃት ሲደርስባቸው የተመለከቱ ሲሆን እርዳታ ለመጠየቅ በሄዱበት ሰዓት ሞተው እንዳገኛቸው ገልፀዋል።

ታዶባ ተብሎ የሚጠራው ጫካ 88 ነብሮች ያሉት ሲሆን፣ ከዚያም በተጨማሪ አቦሸማኔና ሌሎችም እንስሳቶች መኖሪያ ነው ተብሏል።