ኬንያ ሳንቲሞቿ ላይ የነበሩ መሪዎችን በእንስሳት ቀየረች

የፎቶው ባለመብት, Kenya central bank
ኬንያ ከዚህ በፊት የተለመዱ የነበሩትን የቀድሞ መሪዎቿን ምስል ከሳንቲሞች ላይ በማንሳት በእንስሳት ምስሎች መተካት ጀምራለች።
የቀድሞዎቹ ሶስት መሪዎች ማለትም፤ ጆሞ ኬንያታ፣ ዳንኤል አራፍ ሞይ እና ሙዋይ ኪባኪ ከዚህ በኋላ በሳንቲሞች ላይ ምስላቸው እንደማይኖር የተገለጸ ሲሆን፤ በወረቀት ገንዘቦችም ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።
የመሪዎቹ ምስል በሳንቲሞች ላይ የሚታተመው እራሳቸውን ለማስተዋወቅና የመንግሥትን ስልጣን እንደ ግል ሃብታቸው ስለሚቆጥሩት ነው ብለው ብዙ ኬንያውያን ያስባሉ።
አዳዲሶቹ ሳንቲሞች እንደ አንበሳ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔና አውራስ ያሉ የሃገሪቱን ታዋቂ የዱር እንስሳት ምስል እንደሚያካትት ተገልጿል።
የኬንያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ልጅ የሆኑ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንደተናገሩት አዲሶቹ ሳንቲሞች እንደ ትልቅ ለውጥ ሊታዩ የሚገቡና ሃገሪቱ የተጓዘችውን ረጅም ርቀት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሚገርም ሁኔታ በሳንቲሞቹ ላይ ያሉት የሶስቱም የቀድሞ መሪዎች ምስል ፕሬዚዳንቶቹ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በተሰጠ ትዕዛዝ የታተሙ ናቸው።
ሙዋይ ኪባኪ በ2002 በምርጫ አሸንፈው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ምስላቸውን በወረቀት ገንዘብ ላይ እነደማያሰፍሩ ቃል ቢገቡም፤ በመጨረሻ ግን ምስላቸው በሳንቲምና በወረቀት ገንዘብ ላይ እንዲታተም አዝዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኬንያ ዜጎች በመጣ ከፍተኛ ጫና ምክንያት የሃገሪቱ ህገ መንግስት በ2010 እንዲሻሻል የተደረገ ሲሆን፤ የማንኛውም ሰው ምስል በወረቀት ገንዘብና ሳንቲሞች ላይ መታተም የለበትም የሚለው ደግሞ ከማሻሻያዎቹ መካከል አንዱ ነበር።
የሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ይህንን ህግ በሳንቲሞቹ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ በወረቀት ገንዘብ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል።
ማዕከላዊ ባንኩ እንዳስታወቀው አዲሱ የእንስሳት ምስል የበለጸገችና በአዲስ መልክ እየተሰራች ያለችውን ኬንያ በተገቢው ሁኔታ ይገልጻል።












