የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጠው ሜሪ ስቶፕስ ኬንያ ውስጥ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Marie Stopes Kenya
በዓለማቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት የሚሰጠው ሜሪ ስቶፕስ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አገልግሎት በኬንያ ባለስልጣናት ታገደ።
የጤና ባለሙያዎች ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ድርጅቱ የጽንስ ማስወረድን የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎችን ሰርቷል የሚሉ ከፍተኛ ቅሬታዎች ሲነሱበት ቆይቷል ብሏል።
ኬንያ ውስጥ የእናትየው ጤና አደጋ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ጽንስ ማቋረጥ በህግ ያስቀጣል።
ሜሪ ስቶፕስ በበኩሉ እስካሁን ድረስ ስራውን በተገቢውና ህጉን በጠበቀ መልኩ ሲሰራ እንደነበር አስታውቋል።
የኬንያ የማስታወቂያ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት አልፍሬድ ሙቱዋ እገዳው ተገቢ እንደሆነ በመግለጽ ጽንስ ማስወረድ በቀድሞ የአሜሪካ መንግስት አበረታችነት የመጣና ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ያስከተለ ተግባር ነው ብለዋል።
አንዳንድ ኬንያውያን ግን እገዳው ህገወጥና ለጤና ጠንቅ የሆነ በየሰፈሩ የሚደረግ የጽንስ ማስወረድን አንዳያበረታታ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
የኬንያ የጤና ባለሙያዎች ምክር ቤት ለሜሪ ስቶፕስ በላከው ደብዳቤ መሰረት ድርጅቱ መልእክቱ ከደረሰው ዕለት ጀምሮ ማንኛውም አይነት የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎቶችን በአስቸኳይ እንዲያቆም አዝዟል።
ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ ለሚቀጥሉት ስድሳ ቀናት የሚሰጣቸውን አገለግሎቶች የሚገልጽ ሙሉ ሪፖርት በየሳምንቱ ለምክር ቤቱ እንዲያስገባም ተጠይቋል።
ሜሪ ስቶፕስ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚለቃቸው ማስታወቂያዎች በመስሪያ ቤታቸው ፍቃድ ያላገኙ እንደሆነና ጽንስ ማቋረጥ ጥሩ እንደሆነ የሚገልጹ ናቸው ሲሉ የማስታወቂያ ጉዳዮችን የሚቆጣጠሩት አልፍሬድ ሙቱዋ ተናግረዋል።
ድርጅቱ የሃገሪቱን ህገመንግስት በጠበቀ መልኩ አግልግሎት ሲሰጥ እንደነበረ በኬንያ የሜሪ ስቶፕስ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዳና ቲልሰን ገልጸዋል።
ሜሪ ስቶፕስ ኬንያ፤ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር አገልግሎት መስጠት የጀመረው እ.አ.አ. በ1985 ሲሆን፤ 22 ክሊኒኮችና 15 ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መስጫዎች አሉት።












