አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ-ኢትዮጵያ ሴት ርዕሰ ብሔር አገኘች

ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር በመሆን በዛሬው ዕለት ተሹመዋል። አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት አምባሳደር ሳህለወርቅ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በወርሃ የካቲት 1942 የተወለዱ ሲሆን ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛና አማርኛ አቀላጥፈው የይናገራሉ።

አምባሳደር ሳህለወርቅ የፈረንሳዩ ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሩቅ ሲሆኑ እኤአ ከ1989-1993 ተቀማጭነታቸውን ሴነጋል በማድረግ የማሊ፣ የኬፕ ቨርድ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የጋምቢያና የጊኒ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ

የፎቶው ባለመብት, FBC/Screenshot

የምስሉ መግለጫ, ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ

እኤአ ከ1993-2002 ደግሞ በጅቡቲ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን በወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቋሚ ተወካይም ነበሩ።

ከዚያም በመቀጠል ከ2002-2006 በፈረንሳይ አምባሳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ተወካይ ሆነው ሰርተዋል።

በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ውስጥ የተቀናጀው የሰላም አስከባሪ ሃይል ተወካይ በመሆን በሴንትራል አፍሪካ(BINUCA) ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ውስጥና በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥም የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሰርተዋል።

እኤአ በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ የነበሩት ባን ኪሙንም በኬኒያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል አድርገው ሾመዋቸው አገልግለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ

የርዕሰ ብሔሯ የመጀመርያ ንግግር

አዲሷ ርዕሰ ብሔር በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክርቤት አባላት ፊት ቃለ መሀላ ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ስለ ሰላም እና ስለ ሴት ልጆች እኩልነት አፅንኦት ሰጥትው ተናግረዋል።

ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ በንግግራቸው የቀድሞው ርዕሰ ብሔር በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን በመልቀቃቸው አመስግነው ይህ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ያልተለመደ ነገር በሀገራችን እየተለመደ መምጣቱንና ለለውጥና ለተስፋ ዕድል መሰጠት መጀመሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ይህም አሉ ርዕሰ ብሔሯ ባደጉና በሰለጠኑ ሀገራት እንደተለመደው "ከያዝነው ሥልጣንና ኃላፊነት በፊትም ሆነ በኋላ ሕይወት የሚቀጥል መሆኑን መረዳታችንን ያሳያል" ብለዋል።

ይህ ለሌሎች ዕድል የመስጠት አርአያነት በተለያዩ እርከኖችና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ርዕሰ ብሔሯ ጨምረውም ታላቅ ሀገር የመገንባት ህልማችንን እውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም በማለት ስለሰላም አበክረው ተናግረዋል።

"በሰላም እጦት ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶች በመሆናችን በዚህ የኃላፊነት ቆይታዬ አብይ ትኩረቴ መላው የኢትዮጵያን ሴቶችንና... ሰላም ወዳድ ዜጎችን ከጎናቸው በማሰለፍ ሰላም ማስፈን እንደሚሆን ተናግረዋል። በዚህም መላው ሕዝብና የምክር ቤት አባላት ከጎናቸው እንደሚሆኑ ያላቸውን አምነት ተናግረዋል።

ርዕሰ ብሔሯ በንግግራቸው ደጋግመው አፅንኦት የሰጡት ስለ ሴቶች እኩልነት ነው። ይህ ንግግራቸው በዛ ብለው የሚያስቡ ካሉ "ገና ምኑ ተነካና" በማለት የሕዝብ እንደራሴዎችን ፈገግ አሰኝተዋል።

አባታቸው አራት ሴት ልጆች እንዳሏቸው የገለጹት ርዕሰ ብሔሯ ለዚህ እንድበቃ ረድተውኛል ያሏቸውን ወላጆቻቸውን ባሉበት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋቸዋል።