የመንገድ አቅጣጫ እንዳይጠፋብን የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ አቅጣጫ መለየት ያስቸግሮታል? ወይስ ጠፍቼ ይሆን ብለው እራስዎን በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ?
እንግዲያውስ እነዚህ ምክሮች ይጠቅሞት ይሆናል።
1. ጉዞዎን ቀደም ብለው ያስቡት
መሄድ የሚፈልጉበት ሃገር ወይም ማንኛውም ቦታ ከመሄድዎ በፊት የመንገዶቹን ምስሎች ማግኘት ከቻሉ በደንብ ይመልከቷቸው። እራስዎን በእነዚያ መንገዶች ላይ ሲንሸራሸሩ በጭንቅላትዎ ለመሳል ይሞክሩ።
2. ዘና ይበሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጠፋሁ አልጠፋሁ እያሉ የሚጨነቁ ከሆነ ተፈጥሯዊ የሆነውን አቅጣጫ የመለየት ችሎታዎን ያጠፋዋል። ጉዞ ከመጀመርዎ በፊት ቀድመው መዘጋጀትዎ ይህንን ጭንቀት ለመቀነስ ይረዳዎታል።
3. ትኩረት ይስጡ
ጉዞ በሚያደርጉ ጊዜ ስልክ የሚያወሩ ከሆነ፣ የጽሁፍ መልዕክት የሚላላኩ ከሆነ አልያም ስለሌላ ነገር የሚያስቡ ከሆነ፤ አካባቢዎን ለማስተዋል ይቸገራሉ።
ሙሉ ትኩረትዎን በአንድ ሥራ ላይ ብቻ ያድርጉ። ይሄ ደግሞ በጉዞ ወቅት ትኩረትዎ አካባቢዎ ላይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
4. የተለዩ ምልክቶች ይፈልጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እርሶ ከሚያውቁት ነገር ጋር የሚመሳሰል ወይም ለየት ብሎ የሚታይ ነገር በአካባቢዎ ይፈልጉ።
በትልቅ ከተማ ውስጥ ከሆነ ያሉት በአካባቢው በጣም ትልቁን ህንጻ ለይተው በምልክትነት ይያዙት። እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎን ከህንጻው አንጻር ያድርጉት።
5. ወደ ኋላ ይመልከቱ
ብዙ ጊዜ ሰዎች ትኩረታቸውን የሚያደርጉት ከፊታቸው ያሉት ነገሮች ላይ ብቻ ነው። ነገር ግን ወደ ኋላ መመልከት መግቢያና መውጫዎን ለመለየት ይረዳዎታል። ወደ ኋላ መመልከት የጥሩ አቅጣጫ አዋቂዎች መገለጫ ነው ተብሏል።
በተለይ ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ የሚመለሱ ከሆነ ወደ ኋላ መመልከት እጅግ ጠቃሚ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
6. ትውስታዎን ከቦታዎች ጋር ያዛምዱ
ይሄ ዘዴ የሄዱባቸውን ቦታዎች በትክክል ለማስታወስ እጅግ ጠቃሚ ነው።
በተንቀሳቀሱባቸው የተለያዩ ቦታዎች የሰሟቸው ዘፈኖች ቦታዎቹን በትክክል ለማስታወስ እንደሚረዱ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይ ደግሞ በሄዱበት መንገድ የሚመለሱ ከሆነ ሙዚቃ ጥቅም ይኖረዋል።
7. ማስታወሻ ምስል ያስቀሩ
የጎበኟቸውን ቦታዎች ደግመው ለማየት የሚያስቡ ከሆነ በእያንዳንዱ ቦታ ማስታወሻ ምስሎችን ያስቀሩ።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከተንቀሳቃሽ ምስል በተሻለ መልኩ ምስል ማንሳት አቅጣጫዎችን ለመለየት ይረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
8. ጉዞዎትን መለስ ብለው ያስቡት
ጉዞዎን ካጠናቀቁ በኋላ መለስ ብሎ ማሰብ የማስታወስ ችሎታዎን ለመጨመር ይረዳል።
ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ሁሉ ካደረጉ በኋላ አሁንም የማስታወስ ችሎታዎ ካላስተማመንዎት ዘመነኛ ስልክዎን በመጠቀም መግቢያ መውጫዎን ማየት ይችላሉ።
መልካም መንገድ!












