ኢትዮጵያዊያን በህጋዊ መንገድ ለሥራ ሚሄዱባቸው ሦስት አገሮች

የቤት ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, LA

ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች በውጪ ሃገር የሥራ ስምሪት በህጋዊ መንገድ ተቀጥረው ለመስራት የሚችሉባቸው ሃገራት ሦስት ብቻ መሆናቸውንና እነሱም ከመንግሥት ስምምነት ያላቸው እንደሆነ ተገለፀ።

ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳኡዲ አረብያ፣ ኳታርና ጆርዳን ጋር ብቻ የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረሙን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በፃፉት ደበዳቤ አሳውቀዋል።

ከተጠቀሱት የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ውጪ በተለያዩ መንገዶች ለሥራ መጓዝ ህገውጥ እንደሆነና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቁጥጥር እንደሚያደርጉና እርምጃ እንደሚወስዱም ተገልጿል።

ምክትትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፃፉት ደብዳቤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጠቅላይ ኣቃቤ ህግ፣ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የሲቪል አቭዬሽን ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደረጉ የሚያሳስብ ሲሆን፤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርም ግልባጭ ሆኗል።

መንግሥት የሁለትዮሽ ስምምነት ካልፈፀባቸው አገሮች ጋር ምንም ዓይነት የሥራ ስምሪት እንዳይደረግ የተጠቀሱት ተቋማት ቁጥጥር እንዲያደርጉ ኃላፊነት ተሰትቷቸዋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት አዋጅ፤ ሰራተኛን በውጭ ሃገር ለሥራ ማሰማራት የሚቻለው በኢትዮጵያና በተቀባይ ሀገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል።

በዚህም መሰረት፤ ወደ የመካከለኛ ምሥራቅ አረብ ሀገራት የሚደረግ የሥራ ስምሪት ክልከላ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም መነሳቱ ይታወሳል።

የሁለትዮሽ ስምምነት ወደ አልተደረገባቸው ሃገሮች ማለትም ኩዌት፣ ባህሬይ፣ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስ፣ ሌባኖስና ዮርዳኖስ በዘመድ ጥየቃ፣ በጉብኝት፣ በንግድና በመሳሰሉ የቪዛ አይነቶች ከሃገር በመውጣት ሕገ ወጥ የሥራ ስምሪት እየተደረጉ መሆናቸውንና ተገልጿል።

በዚህ በህገ ወጥ መንገድ በሚደርግ የሥራ ስምሪት ዜጎች ለመብት ጥሰት፣ ያለ ክፍያ ለመስራት፣ ለእንግልት፣ ለስቃይና ሲከፋም ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን ደብዳቤው አመልክቷል።

በመሆኑም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ኤጀንሲዎች ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት የሳኡዲ መንግሥት ከ150 ሺህ በላይ ህጋዊ መኖርያና የሥራ ፈቃድ የላቸውም ያላቸውን ሰራተኞች ማባረሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ መካከለኛ ምሥራቅ የሚደረግ የሥራ ስምሪትን በህግ ከልክሎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 መሰረት፤ ወደ ውጭ በመሄድ ለመስራት አንዳንድ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ተቀምጠዋል።

በዚህም መሰረት ተቀጣሪዎች የትምህርት ደረጃቸው ቢያነስ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቁ፣ ለሚሰማሩበት ሥራ የሚያግዛቸው ከቴክኒክን ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት አስፈላጊውን ስልጣና መውሰዳቸው የሚገልፅ የብቃት መናረጋገጫ እንዲሁም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፀደቀ የሥራ ውል ሊኖር ይገባል።

ከዚህ ውጪ የሚደረግ የሥራ ስምሪት ጉዞ ህገ ወጥ መሆኑን አዋጁ አስፍሯል።