በቤኒሻንጉል ጉምዝ ካማሽ ዞን የመሰረታዊ ፍጆታ እጥረት አጋጠመ

በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አራት የካማሽ ዞን አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለአካልና ንብረት ጉዳት እንዲሁም ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ በዞኑ የምግብ ግብዓቶች እጥረት ማጋጠሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የካማሽ ከተማ ነዋሪ ምግብና ሸቀጦች ወደ ከተማዋ መግባት ባለመቻላቸው ሱቆች ሁሉ ባዶ ናቸው ይላል።

"ከተማው ውስጥ ለመንቀሳቀስ ይቻላል፤ ምንም ችግር የለም፤ ነገር ግን በከተማዋ ውስጥ የሚበላ ነገር የለም። ችግሩ የጀመረው ከደመራ በዓል አንስቶ ቢሆንም ሁኔታዎች ተባብሰው ምንም ዓይነት ነገር ካጣን ዘጠነኛ ቀናችን ነው" ሲል ችግር ላይ እንደወደቁ ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አበራ ባየታ ችግሩ ከመስከረም 16 አንስቶ የነበረ ሲሆን በተለይ ከነጆ ካማሽ እና ከጊምቢ ካማሽ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል ይላሉ።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች የሚደርስን ጥቃት፣ ብሔር ላይ መሰረት ያደረገ ጥቃትን መፍራት፤ አሽከርካሪዎችም ንብረቶቻቸውን ወደ አካባቢው ለመላክ መስጋታቸው ምክንያት ነው ብለዋል።

በተለይ ከነጆ ካማሽ መንገዶችም በመቆፈራቸውና በመዘጋታቸው ለመንቀሳቀስ አዳጋች ሆኗል ይላሉ።

በካማሽ ዞን የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለምግብ አቅረቦት እጦት እንደታገለጡ የሚናገሩት ሃላፊው ካማሽ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ያሉ ወረዳዎች የዕለት የምግብ ፍጆታ የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች እጥረት እንዳጋጠማቸው አስረድተዋል።

በዚህም ሳቢያ የክልሉ መንግስት በየአካባቢዎቹ ተገኝቶ ህብረተሰቡን ለማረጋጋት በሄሊኮፍተር ለመንቀሳቀስ እንደተገደደ የገለፁት ኃላፊው አሁንም ከአጎራባች ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

አክለውም ከዞኑ በመሸሽ በአዋሳኝ የኦሮሚያ ከተሞች የተጠለሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት ቢያሳዩም አብዛኞቹ የመጓጓዣ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ይላሉ አቶ አበራ ባየታ።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮቹን ወደ ቀደመው መኖሪያቸው ለመመለስ የትራንፖርት አገልግሎት ለማመቻቸት መወሰኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

በግጭቱ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።