ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በድንበር አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎችን ማንሳት ጀመሩ

የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች የድንበር ጥበቃ ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ወታደሮች በድንበር አካባቢ ተቀብረው የነበሩ ከ800 ሺህ የሚበልጡ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ማጽዳት መጀመራቸውን የሃገራቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የሁለቱም ሃገራት ወታደሮች በሚንቀሳቀሱባት በደቡብ ኮሪያ የምትገኘው ፓንሙጆም መንደር የተጀመረው የማጽዳት ሥራ የተሳካ እንደነበር ተገልጿል።

እዚህ ውሳኔ ላይ ተደረሰው ሁለቱ የኮሪያ መሪዎች ኪም ጆንግ ኡን እና ሙን ጄ ኢን ባለፈው ወር ፒዮንግያንግ ውስጥ ከተስማሙ በኋላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የታጠቁ ኃይሎች ፊት ለፊት ሆነው ድንበር የሚጠብቁበት የወታደራዊ ቀጠና በሚቀጥሉት 20 ቀናት ውስጥ ነጻ እንደሚሆን የደቡብ ኮሪያው መከላከያ ሚኒስትር ገልጸዋል።

ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ በድንበሮቹ በቅርብ ርቀት የሚገኙት የጥበቃ ቤቶች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎችን በማንሳት ያልታጠቁ ወታደሮችን ብቻ በቦታዎቹ ለማስቀመጥም ታስቧል።

ባለፈው ሚያዚያ ደቡብ ኮሪያ በድንበር አካባቢ ትላልቅ የድምጽ ማጉያዎችን በመጠቀም ስታስተላልፋቸው የነበሩትን ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳዎች እንደምታቆም ገልጻ ነበር።

ወታደራዊ ቀጠናው 250 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 4 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና እስከ ኮሪያ ሰርጥ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፤ እጅግ ከባድ በሚባሉ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችና የጠበቃ ካሜራዎች የታጠረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ወታደሮች በሁለቱም የድንበሩ አካባቢዎች ጥበቃ ያደርጋሉ።

ባለፈው ህዳር ወር አንድ የሰሜን ኮሪያ ወታደር ቀጠናውን በማለፍ ወደ ደቡብ ለማለፍ ሲሞክር በራሱ ሃገር ወታደሮች ተተኩሶበት መቁሰሉ ይታወሳል።