አኳሪየስ፦ ከሊቢያ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞችን የምትታደገው መርከብ ፈቃዷን ተነጠቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አኳሪየስ ትባላለች፤ በሜድትራኒያናን ባህር ላይ በመንሸራሸር ስደተኞችን የመታደግ ሥራ በመሥራት ነው የምትታወቀው።
ከሊቢያ ወደ አውሮፓ የሚሸጋገሩ ስደተኞችን የመታደግ ሥራ የምትሠራው አኳሪየስ ፈቃዷን በመነጠቋ ምክንያት ሌላ ፈቃድ እስኪሰጣት ድረስ መንቀሳቀስ አትችልም።
በሜድታራንያን ባህር ላይ በመንቀሳቀስ መሰል ስደተኞችን የመታደግ ሥራ ከሚሰሩ የግል መርከቦች የመጨረሻዋ ነበረች አኳሰሪየስ።
የመርከቧ ባለቤት የሆነው የተራድዖ ድርጅት የጣልያን መንግሥት ነው የአኳሪየስ ፈቃድ እንዲነጠቅ ያደረገው የሚል ክስ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
መርከቧ በፓናማ ባንዲራ ስር ሆና ነበር ሜድትራኒያን ባህር ላይ በመንቀሳቀስ ስደተኞችን ትታደግ የነበረው።
የፓናማ መንግሥት መርከቧ ፖለቲካዊ ችግር እያስከተለች በመሆኗና የጣልያን መንግሥት ፈቃዷን እንድንሰርዝ በወተወተን መሠረት ነው ይህን ልናደርግ የተገደድነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የጣልያን የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ ግን እኛ የፓናማ መንግሥትን ጫና ውስጥ አልከተትንም ብለዋል። ምንም እንኳ አንድ ሰሞን መርከቧን 'የስደተኞች ታክሲ' ሲሉ መጥራታቸው ባይዘነጋም።
ሚኒስትር ማቴዎ በስደተኞች ጉዳይ ጠንካራ ቀኝ ዘመም አቋም በማፀባረቅ ይታወቃሉ።
ከአኳሪየስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ስደተኛ ታደጊ መርከበኞች ጋር እሰጥ-አገባ በመግባትም ይታወቃሉ።
የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓውያኑ 2018 ብቻ 1700 ገደማ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመጋባት በሚደረግ ሙከራ ህይወታቸውን አጥተዋል።
አኳሪየስ ከወራት በፊት ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ሲሸጋገሩ የነበሩ በርካታ አፍሪቃዊ ስደተኞችን በመታደጓ ምክንያት የዜና መክፈቻ ሆና እንደነበር አይዘነጋም።












