ተመድ ቻይና ''ሙስሊሞችን በጅምላ መያዟ » አሳስቦኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፀረ ሽብር ርምጃ ሰበብ የተያዙትን የቻይና የዩጉሁረስ የጎሳው አባላት እንዲፈቱ ጠየቀ።
ቻይና ቁጥራቸው 1 ሚሊየን የሚሆኑ፣ በምዕራብ ዣንግጂያንግ ክልል የሚኖሩ ሙስሊም የዩጉሁረስ ጎሳ አባላትን በ «መልሶ ማስተማር» ጣቢያዎች ውስጥ ማጎሯን የሚያሳይ 'ሪፖርት' መውጣቱን ተከትሎ ነው ተመድ ድምፁን ያሰማው።
ቤጂንግ አቤቱታውን ብትቃወምም የተወሰኑ የሃይማኖት አክራሪዎች ለ«መልሶ ማስተማር» ዓላማ እንደያዘች አምናለች።
ቻይና እስላማዊ ፅንፈኞች እና ተገንጣዮች የግዛቱን ሰላም እያደፈረሱ እንደሆነ በማንሳት ትከሳለች።
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ የተመድ የዘር አድሎ አስወጋጅ ኮሚቴ አባላት ፣«ቻይና የዩጉሁረስ ራስ- ገዝ ግዛትን ግዙፍ የሰቆቃ ጣቢያ ወደ ሚመስል ሁነት ቀይረዋለች» በማለት ምልከታቸውን አጋርተዋል።
ቻይና ግን የጎሳው አባላት ሙሉ መብት እንዳላቸው በማንሳት ፣«በሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት የተታለሉ» ወገኖች ግን በመልሶ ማስፈር እና ማስተማር ሊታገዙ ይገባል ብላ እንደምታምን አስታውቃለች።












