ሙስጠፋ ኡመር የሶማሌ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

ሙስጠፋ ኡመር

የፎቶው ባለመብት, Addis Standard

አቶ ሙስጠፋ ኡመር ጊዜያዊ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ።

አቶ ሙስጠፋ ኡመር የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲመሩ የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደመረጣቸው አዲስ አበባ የሚገኘው የቢቢሲ ሶማልኛ ሪፖርተር አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን ለበርካታ ዓመታት የመሩትን አቶ አብዲ ሙሐመድ ኡመርን በመተካት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ክልሉን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ አህመድ አብዲ ሞሐመድ፤ አቶ ሙስጠፋ የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን አረጋግጠዋል።

አቶ አህመድ፤ አቶ ሙስጠፋ የሶማሌ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ተደርገው መሾማቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። አዲሱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት የሶህዴፓ አባል ባይሆኑም ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ የፓርቲው ሕገ-ደንብ እንደሚፈቅድላቸው አክለዋል።

አቶ ሙሰጠፋ ከክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነታቸው በተጨማሪ የሶህዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ተደርገውም ተሹመዋል። የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሺዴ የሶህዴፓ ሊቀመንበር ተደርገው መሾማቸው ይታወሳል።

አቶ ሙስጠፋ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሐመድ ኡመር የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማሉ በማለት በተደጋጋሚ በመተቸት ይታወቃሉ።

ከሳምንታት በፊት አቶ አብዲ ከሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን ጋር አድርገው የነበረው ቆይታ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በወቅቱ አቶ አብዲ ከተናገሩት የብዙዎችን ቀልብ ይዞ የነበረው፤ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን በሚመለከት የሰጡት አስተያየት ነበር። ''ጌታቸው ሙሰኛ፣ ሌባ እና ራሰ ወዳድ ነው'' ብለው ነበር።

ይህን አስተያየታቸውን ተከትሎ ከሳምንታት በፊት አቶ ሙስጠፋን አነጋግረናቸው ነበር። በወቅቱ ራሳቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ብለው የሚጠሩት አቶ ሙስጠፋ፤ አቶ አብዲ በቅርቡ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት እንዲነሱ የተደረጉት አቶ ጌታቸውን በከፍተኛ ደረጃ መውቀስ ለምን አስፈለጋቸው? የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር።

አቶ ሙስጠፋ በምላሹ፤ አቶ አብዲ ይህን መሰል ወቀሳን መሰንዘር ያስፈለጋቸው፤ "የአዲሱ የፖለቲካ ለውጥ አካል ሆነው ስልጣን ላይ መቆየት ስለሚፈልጉ ነው። አቶ ጌታቸው እና ሌሎች ግለሰቦች ይፈጽሙ የነበሩትን በይፋ ማውጣት 'ተዓማኒነትን ያተርፍልኛል' የሚል ስሌትን በመያዝ ያደረጉት ነገር ነው'' ብለውን ነበር።

"ከቀናት በፊት የክልሉ ምክር ቤት ተሰብስቦ ባለበት ወቅት አቶ አብዲ አንድ ጥቁር ቦርሳ ይዘው መጡ። ከዚያም 'በዚህ ሻንጣ ውስጥ በርካታ ሚስጥሮች አሉኝ። የክልሉ ባለስልጣናት እና የፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት ሚስጥር እዚህ ውስጥ አለ። ገንዘብ የከፈልኳቸው ባለስልጣናት አሉ። እኔን ቢነኩ ይህን ሚስጥር አወጣለሁ' በማለት ሲያስፈራሩ ነበር'' በማለት ተናግረውም ነበር።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አብዲ ከስልጣናቸው ከተነሱ ሁለት ሳምንታት አልፈዋል።

አቶ አብዲ ከክልል ፕሬዚዳንትነታቸው መነሳታቸው ከተሰማ ከሁለት ቀናት በኋላ አህመድ አብዲ ሼክ ሞሃመድ (ኤልካስ) ፕሬዚዳንት ተደርገው ተሹመው ነበር።