የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ ስጋት የፈጠረባት አሜሪካ ማሳሰቢያ ሰጠች

የአሜሪካ መንግሥት የቴክኖሎጂ ተቋማት አዲሱ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ ሕዝቡን እንዲጠብቁ አሳሰበ።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በአገሪቱ ያሉ የታላላቅ ቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎችን ሐሙስ ዕለት በመጥራት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስለደቀነው ስጋት ባማከራቸው ወቅት ነው ይህ ማሳሰቢያ የተሰጠው።

ከጉግል ሱንዳር ፒቻይ፣ ከማይክሮሶፍት ሳትያ ናዴላ እና ከኦፕንኤአይ ሳም አልትማን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሊያስከትል ከሚችላቸው አደጋዎች ማኅበረሰቡን የመጠበቅ “የሞራል” ግዴታ እንዳለባቸው ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ተነግሯቸዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍን የሚቆጣጠር ሕግ ሊያወጣ እንደሚችልም አሳውቋል።

በቅርቡ ይፋ የተደረጉት የሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑት ቻትጂፒቲ እና ባርድ በሕዝቡ ውስጥ ሰፊ መነጋገሪያ መሆናቸው የአሜሪካ መንግሥት ስለ ቴክኖሎጂው ሳያሳስበው አልቀረም።

እነዚህ አዲስ ቴክኖሎጂዎች በሰከንዶች ውስጥ የተለያዩ ምንጮች በመጠቀም አንድ ሰው የሚጠይቃቸውን መረጃዎች የሚያቀርቡ ናቸው። በዚህም በአንድ ሰው የተዘጋጁ የሚመስሉ የኮምፒውተር ኮዶች መቀመር፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎችን ማቅረብ እንዲሁም ግጥሞችን ሳይቀር መጻፍ የሚችሉ ናቸው።

የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሚኖረው ሚና ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ ጉዳቱ እና ጥቅሙን በማንሳት በስፋት ክርክር እየተደረገ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ለምክክር የተጠሩት የቴክኖሎጂ ተቋማት “ምርቶቻቸው ደኅንነታቸው የተጠበቀ እና ጉዳት የማያስከትሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ” እንዳለባቸው ያሳሰበ ሲሆን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በተመለከተ አዲስ ሕግ እና ደንብ ለማውጣት በሩ ክፍት እንደሆነ አመልክቷል።

ቻትጂፒቲን የሰራው ኦፕንኤአይ የተባለው የቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን፣ ሕግ ማውጣትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ኃላፊዎች በአስፈላጊነቱ ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ እንዳላቸው ገልጿል።

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ካማላ ሃሪስ ዋይት ሐውስ ውስጥ ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ባወጡት መግለጫ፣ ምንም እንኳን አዲሱ ቴክኖሎጂ ጠቃሚ ገጽታዎች ቢኖሩትም በደኅንነት፣ በግል መረጃ ጥበቃ እና በመብቶች ላይ አደጋን ሊደቅን ይችላል ብለዋል።

የግሉ የቴክኖሎጂ ዘርፍም እንዲህ ያሉት ምርቶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ከማረጋገጥ አንጻር “የሥነ ምግባር፣ የሞራል እና የሕግ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል ሃሪስ።

የአሜሪካ መንግሥት ሰባት አዳዲስ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስችል 140 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን አስታውቋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሕግ መተዳደር አለበት በማለት ከፖለቲከኞች እና ከቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎች እየቀረበ ያለው ጥሪ እየተጠናከረ እየመጣ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አባት ናቸው የሚባሉት ጄፍሪ ሂንተን፣ በዘርፉ ውስጥ ባበረከቱት ሥራ እንደሚጸጸቱ በመግለጽ ጉግል ውስጥ የነበራቸውን ሥራ ለቀዋል።

ሂንተን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ውስጥ ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚያስከትሉት አደጋ “በጣም አስደንጋጭ ነው” ብለዋል።

ባለፈው መጋቢት ላይ ኤሎን መስክ እና የአፕል መስራች ስቲቭ ዎዝኒያክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል።

ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ የፈጠረው ሌላኛው ስጋት ደግሞ በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት የተነሳ በሰዎች የሚሰሩ ሥራዎችን በመረከብ ሥራ አጥነት ሊፈጥር ይችላል የሚል ነው።

በተጨማሪም ቻትጂፒቲ እና ባረድ የተባሉት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ትክክለኛነታቸው አጠያያቂ ሊሆን ስለሚችል የአሳሳች መረጃ ስርጭትን ሊያስፋፉ ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል።

የቅጂ መብት ጉዳይ (ኮፒራይት) ጥሰትን፣ ድምጽ በማስመሰል ማጭበርበር ሊስፋፋ እና የቪዲዮ ምስሎችን በመፍጠር የሐሰት ዜና እንዲስፋፋ በር ይከፍታል ተብሏል።

ነገር ግን ቢል ጌትስን የመሳሰሉ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ደጋፊዎች ደግሞ ቴክኖሎጂው ለተወሰነ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን መጠየቁ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን “ችግር አይፈታውም” በማለት ይከራከራሉ።

ከዚያ ይልቅ ግን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል በሚለው ላይ ማተኮር ይገባል በማለት ጌትስ ይመክራሉ።