ለቻይና ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለመስጠት ሞክሯል የተባለ የአሜሪካ የቀድሞ ወታደር ተያዘ

አንድ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የቀድሞ አባል ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለቻይና የስለላ ድርጅት አሳልፎ ለመስጠት ሲሞክር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።

የቀድሞው ወታደር ሊያዝ የቻለው በኢንተርኔት አማካይነት ስለቻይና የስለላ ድርጅት መረጃዎችን ሲያፈላልግ ተደርሶበት መሆኑ ተገልጿል።

የ29 ዓመቱ የመቶ አለቃ ጆሴፍ ሽሚት በቁጥጥር ስር የዋለው ከሆንግ ኮንግ ተነስቶ አሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ አየር ማረፊያ ሲደርስ ነው።

የዋሽንግተን ግዛት የፌደራል መንግሥቱ ዐቃቤ ሕግ ቴሳ ጎርማን፣ ወታደሩ “ምሥጢር አሳልፎ በመስጠት በአገሩ ላይ ክህደት ለመፈጸም ያደረገው ጥረት የሚያስደነግጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ምሥጢራዊ መራጃዎችን ለቻይና አሳልፎ ለመስጠት ሞክሯል የተባለው ሽሚት በአሜሪካ ጦር ኃይል ውስጥ በመደበኛ ወታደርነት ከአውሮፓውያኑ 2015 አስከ 2020 ድረስ ሲያገለግል ነበር።

ወታደሩ በአብዛኛው አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው በአሜሪካ መንግሥት ብርቱ ተብለው የተለዩ የመከላከያ ምስጢሮችን ሊያገኝ በሚችለበት በምዕራብ ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኘው ልዊስ-ማኮርድ ወታደራዊ ሠፈር ውስጥ ነበር።

የአሜሪካንን ብሔራዊ የደኅንነት ምሥጢሮች ለቻይና አሳልፎ ለመስጠት ያደረገው ሙከራ የተዘረዘረበት የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚለው፣ ጆሴፍ ሽሚት በርካታ ሰነዶችን አዘጋጅቷል፣ ብዙ መረጃዎችንም በጉግል ላይ ፍለጋ ማድረጉ ተጠቅሷል።

ግለሰቡ በጉግል ላይ መረጃ ለመፈለግ ባደረገው ጥረት ውስጥ እንዴት አሜሪካንን ከድቶ ወደ ቻይና መግባት እንደሚችል እና ለቻይና የደኅንነት መሥሪያ ቤት እንዲሁም ቱርክ በሚገኘው የቻይና ቆንስላ ውስጥ “በመርማሪነት” መሥራት እንደሚችል ያለውን ፍላጉት አመልክቷል።

በተጨማሪም ኢስታምቡል ለሚገኘው የቻይና ቆንስላ በጻፈው ኢሜይል ላይ “ከፍተኛ ምሥጢሮችን የማግኘት ፈቃድ አለኝ፣ የሚቻል ከሆነ ከቻይና መንግሥት አንድ ሰው አግኝቼ ያሉኝን መረጃዎች ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ” ማለቱ ተጠቅሷል።

ወታደሩ “ከፍተኛ ምሥጢሮች” በሚል ርዕስ በማይክሮሶፍት አማካይነት ሰነድ አዘጋጅቷል ተብሎም ክስ ቀርቦበታል።

ዐቃቤያነ ሕጎች እንዳሉት 23 ገጾች ያሉት ሰነድ ርዕሱ በቻይንኛ ቋንቋ ቢጻፍም “አብዛኛው በውስጡ የያዛቸው መረጃ ግን በእንግሊዝኛ የተጻፉ ናቸው።”

ሌላኛው የተገኘበት ሰነድ ደግሞ “ለቻይና መንግሥት የሚሰጥ ጠቃሚ መረጃ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል።

መርማሪዎች እንዳሉት ተጠርጣሪው ሰላዮች ምን እንደሚሠሩ እና እንዴት እንደሚመለመሉ የሚያስረዱ ከስለላ እና ከደኅንነት መረጃ ጋር የተያያዙ ድረ ገጾችን ጎብኝቷል።

ወታደሩ በሠራዊቱ ውስጥ የሚሰጠው የአገልግሎት ጊዜ ሲጠናቀቅ ወደ ቻይና ከመሄዱ በፊት ቱርክ ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ቆይቷል። ከዚያም በኋላ አርብ ዕለት ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ አስከተያዘበት ጊዜ ድረስ ወደ አሜሪካ ሳይመለስ መቆየቱ ተነግሯል።

ዐቃቤ ሕግ ቴሳ ጎርማን “የሠራዊታችን አባላት አገራችንን እና ሕገ መንግሥቷን ለመጠበቅ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። ነገር ግን ይህ የቀድሞ የሠራዊት አባል የፈጸመው ድርጊት አስደንጋጭ ነው” ብለዋል።

ወታደሩ “ብሔራዊ የመከላከያ መረጃን አሳልፎ ለመስጠት መሞከሩ ብቻ ሳይሆን፣ ተቀናቃኝ አገር ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የመከላከያ መሥሪያ ቤት የኮምፒውተር መረብ ዘልቆ እንዲገባ የሚያስችል መረጃን ለመስጠት ሞክሯል” በማለት በከባድ ወንጀል መጠርጠሩን ተናግረዋል።

ጆሴፍ ሽሚት ብሔራዊ የመከላከያ መረጃን በመያዝ እና አሳልፎ ለመስጠት በመሞከር ክስ ተመስርቶበታል። ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በአስርታት የሚቆጠር እስር ሊፈረድበት ይችላል።

በተመሳሳይ ከሁለት ወራት በፊት በደቡብ ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኝ የጦር ሠፈር የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላት ለቻይና በመሰለል ተጠርጥረው መያዛቸው ይታወሳል።

ሁለቱ ሰዎች የመርከቦችን እና የራዳር ንድፎችን እንዲሁም ዝርዝር የቴክኒክ መረጃዎችን ለቻይና አሳልፈው በመስጠት በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ተከፍሏቸዋል ተብለው ተከሰዋል።