ኮሎምቢያዊው ዋነኛ የዕጽ አዘዋዋሪ በአሜሪካ እስር ቤት ሕይወቱ አለፈ

በአንድ ወቅት ስመ ገናና የነበረውና ካሊ የተሰኘው የኮሎምቢያ የአድንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ በዩናይትድ ስቴትስ ማረሚያ ቤት ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።

ጊልቤርቶ ሮድሪጌዝ ኦሬዉላ በአንድ ወቅት ከዓለም የኮኬይን ንግድ አብዛኛውን መቆጣጠር ከመቻሉ ባለፈ የፓብሎ ኤስኮባር ዋና ተቀናቃኝ ለመሆን በቅቶ ነበር።

የ83 ዓመቱ አዛውንት ከተቀናቃኞቹ እና ከሕግ አካላት አንድ እርምጃ ቀድሞ በመገኘት ብቃቱ ምክንያት 'የቼዝ ተጫዋች' የሚል ቅጽል ስም እስከማግኘት በቅቷል።

እአአ በ1995 ዕድል አብራው ያልነበረችው ጊልቤርቶ ኮሎምቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ። በ2004 ደግሞ ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ።

የቀድሞው የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መሪ የ30 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ይገኝበት በነበረው በሰሜን ካሮላይና ማረሚያ ቤት በህመም ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።

ጊልቤርቶ ሮድሪጌዝ ኦሬዉላ ዝናው በናኘበት ወቅት ከወንድሙ ሚጌል ጋር የካሊ አደንዛዥ ዕጽ ቡድን ዋነኛ መሪ ነበር።

እንደአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር (ዲኢኤ) ከሆነ ወንድማማቾቹ የካሊ መሪዎች በ1990ዎቹ አጋማሽ ከዓለም አጠቃላይ የኮኬይን ንግድ 80 በመቶውን ይቆጣጠሩ ነበር።

ንግዱን በብቸኝነት መቆጣጠር የቻሉት እአአ በ1993 የረዥምጊዜ ተቀናቃኛቸው የነበረው የሜድሊን ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ፓብሎ ኤስኮባር በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ነው።

ኤስኮባር የሚመራው ካሊ ኮሎምቢያ ውስጥ አመፅ በማነሳሳት ለመፈራት በቅቶ ነበር። የሮድሪጌዝ ኦሬዉላ ወንድማማቾች ደግሞ ራሳቸውን እንደ ተከበሩ ነጋዴዎች ለመሳል ሞክረዋል።

በኋላም እጅ መንሻ በመስጠት ከፖለቲከኞች ጋር ወዳጅ ለመሆን መብቃታቸውን ገልጸዋል። የነበራቸው ወዳጃዊ ግንኙነት እንደ ሜዴሊን ተቀናቃኞቻቸው በባለሥልጣናት ክትትል ስር እንዳይገቡ አድርጓቸዋል።

በተግባር ግን ካሊ ርህራሄ የለሽ ጨካኝ ቡድን ነበር። አባላቱ ለዓመታት ትርፋማውን የኮኬይን ገበያን ለመቆጣጠር ከሜዴሊን ባላንጣዎቻቸው ጋር ተዋግተዋል።

የሮድሪጌዝ ኦሬዉላ ወንድማማቾች ቦምቦችን እና ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችን ጭምር አሰማርተዋል። ከ60 ለሚበልጡ የፓብሎ ኤስኮባር ዘመዶች እና አጋሮች ሞት ተጠያቂ ከሆነው የፔፔ ቡድን ጀርባም እንደነበሩ ይታመናል።

እአአ በ1980ዎቹ በኮሎምቢያ በነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ አባላት፣ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች እና ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።

የካሊ ቡድን ፍጻሜ በ1995 ላይ የጀመረው ፖሊሶች ጊልቤርቶ ሮድሪጌዝ ኦሬዉላን ካሊ በሚገኘው የቅንጦት መኖሪያ ቤቱ በቁጥጥር ስር ካዋሉት በኋላ ነው። በወቅቱ የልብስ ቁም ሳጥን ውስጥ ተደብቆ መያዙ ተነግሮ ነበር።

በተያዘ በአንድ ዓመት ውስጥ ከቡድኑ ሰባት መሪዎች መካከል ስድስቱ ሞተዋል አልያም እስር ቤት ተወርውረዋል።

ታናሽ ወንድሙ ሚጉዌል በበኩሉ ጊልቤርቶ ከተያዘ ከሁለት ወራት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል።