በእስራኤል-ሐማስ ዙሪያ ሐሰተኛ መረጃዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ የአውሮፓ ህብረት ሜታን ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ “ሐሰተኛ መረጃዎች” በሜታ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመስፋፋቱ የአውሮፓ ሕብረት ማርክ ዙከርበርግን አስጠነቀቀ።
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ ምላሽ ለመስጠት እና የአውሮፓን ሕግ ለማክበር 24 ሰዓታት ተሰጥቶታል።
የማሕበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በግጭቱ ዙሪያ በበርካታ ሐሰተኛ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ተጥለቅልቀዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ማክሰኞ ዕለት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ለኤክስ (ቀደም ሲል ትዊተር ተብሎ ለሚጠራው) አስተላልፏል።
የሕብረቱ የዘርፉ ኃላፊ ቲዬሪ ብሬተን “ወቅታዊ፣ ተገቢ እና ተጨባጭ እርምጃ” መውሰዱን ማረጋገጥ እንዳለበት ለሜታ አስታውቀዋል።
በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው ኩባንያው በመድረኩ ላይ ያለውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመግታት ስለወሰዳቸው "ተመጣጣኝ እና ውጤታማ" እርምጃዎች እንዲያሳውቅ 24 ሰዓታት ተሰጥቶታል።
የሜታ ቃል አቀባይ “ሐማስ በእስራኤል የፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በፍጥነት ተለዋዋጭ የሆነውን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል እና ምላሽ ለመስጠት፣ ኢብራይስጥ እና አረብኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ባለሙያዎችን ያካተተ ልዩ ማዕከል በፍጥነት አቋቁመናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ቡድኖቻችን የማህበራዊ ሚዲያዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ፖሊሲዎችን ወይም ሕጎችን የሚጥሱ ይዘቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመገደብ መሥራታችንን እንቀጥላለን። ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽኑ በበኩሉ በአውሮፓ ሕብረት የሽብር ቡድን ተብሎ በተሰየመው ከፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ጋር የተገናኙ ጎጂ ይዘቶች እንዳይሰራጩ የመጠበቅ ሕጋዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሁሉንም የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች አስታውሷል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ "በበድረገጽ የሚሰራጩና ከሐማስ ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች ለሽብርተኝነት ይዘት ብቁ ናቸው። ሕገ ወጥም ናቸው። በመሆኑም በዲጂታል አገልግሎቶች ሕግ እና በአሸባሪዎች የበይነ መረብ ይዘት ደንብ መሠረት መወገድ አለባቸው" ብለዋል።
የመስክ ማስጠንቀቂያ
ብሬተን ማክሰኞ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም “አመጽ እና የአሸባሪነት ይዘት” ያላቸው ጉዳዮች ከኤክስ ላይ አልወረዱም ሲሉ ለኤሎን መስክ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
መስክ ኩባንያቸው ከሐማስ ጋር የተቆራኙ አዳዲስ የተፈጠሩ አካውንቶችን ማስወገድን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግሯል። አሉ ያላቸውን ጥሰቶች እንዲዘረዝርለትም የአውሮፓ ሕብረትን ጠየቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ብሬተን ለመስክ በጻፉት ደብዳቤ አሉ ስለተባሉት የሐሰተኛ መረጃዎች በዝርዝር አልገለጹም።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ "ሐሰተኛ እና የተጭበረበሩ ምስሎች እና መረጃዎች" በስፋት ሲዘገቡ እንደነበር ግን ተናግረዋል።
"አሰራሮቻችሁ ውጤታማ መሆናቸውን በአስቸኳይ እንድታረጋግጡ እና ስለተወሰዱት እርምጃዎች ለቡድኔ እንድታሳውቁ እጋብዛለሁ" ሲሉ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ደብዳቤ ላይ ጽፈዋል።
ይህ ሆነው ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከገደለ እና በደርዘን የሚቆጠሩን ደግሞ አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
በምላሹም የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽሞ ከ900 በላይ ሰዎችን ገድሏል።
መስክ በኤክስ ላይ በሰጠው ምላሽ “በእኛ ፖሊሲ ሁሉም ነገር ክፍት እና ግልጽ ነው። ይህንንም የአውሮፓ ሕብረት እንደሚደግፈው አውቃለሁ” ብሏል።
"እባክዎ በኤክስ ላይ የጠቀሷቸውን ጥሰቶች ሕዝብ እንዲያያቸው ይዘርዝሩ" ሲልም አክሏል።
የአውሮፓ ሕብረት ዲጂታል አገልግሎቶች ሕግ የትልልቅ ማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ለመጠበቅ የወጣ ነው።
ባለፈው ህዳር ወር ሕግ ሆኖ ቢጸድቅም ድርጅቶቹ ሕጉን ስለማከበራቸው ለማረጋገጥ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
ሕጉን አለማክበር እስከ 6 በመቶ የሚደርስ የድርጅቱን ገቢ እንዲከፍል ወይም የአገልግሎቱን መቋረጥ ሊያስከትልበት ይችላል።
መስክ ኩባንያውን እአአ በ2022 ከገዛ በኋላ የትዊተርን የደህንነት ምክር ቤት አፈረሰ። በ2016 የተመሰረተው የበጎ ፈቃድ ምክር ቤት 100 የሚጠጉ ገለልተኛ ቡድኖችን የያዘ ሲሆን እንደ ልጆችን ማጎሳቆልና የጥላቻ ንግግርን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ይመክር ነበር።












